Tuesday, January 17, 2012

አንብቦተ መጽሐፍ በቅዱስ ኤፍሬም


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
08/05/2004
አዲስ አበባ

           ቅዱስ ኤፍሬም ስለአንብቦተ መጽሐፍ  ፖፕሊየስ ለሚባል ወዳጁ በጻፈው ደብዳቤው ላይ እንዲህ ብሎ እናገኘዋልን፡-
“ንጹሕ መስታወት የሆነውን የጌታችንን ቅዱስ ወንጌል በእጅህ መያዝን ስላልተውክ መልካምን አደረግህ ፡፡ በእርሱ መስታወትነት ማንም ምን መምሰል እንዳለበት ይረዳበታል ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ወገኖች በዚያ ውስጥ ምስላቸውን ከማግኘታቸው በተጨማሪ የራሳቸውን ተፈጥሮ በማስተዋል ከነውር እንዲጠበቁትና በቅድስና ጸንተው ያለመለወጥ እንዲመላለሱ ይረዳቸዋል ፡፡ በሰውነታቸውም ላይ ነውር አይገኝም ፤ ከእድፍም የጸዱ ይሆናሉ ፡፡
በመስታወት ፊት ባለቀለም ቁስ ቢቆም እንደቀለሙ ዓይነት እንዲሁ መስታወቱ ይሆናል ፡፡ ነገር ግን የመስታወቱ  ባሕርይው አይቀየርም ፡፡ ነጭ የሆነ ቁስ በፊቱ ቢያቆሙ ያንኑ ነጭ ቁስ መልሶ ያሳየናል ፡፡ ጥቁር ቀለም ያለው ቁስ በፊቱ ቢቆም የጥቁረቱን መጠን ያሳየዋል ፡፡ ቀይ ከሆነም ቅላቱን ያሳየዋል ፡፡ ውብ ገጽታ ካለው ደግሞ ውብቱን ያሳየዋል ፡፡ መልከጥፉም ከሆኑ እንዲሁም ለዐይን ምን ያህል እንደሚያስቀይሙ ያሳያቸዋል ፡፡ እያንዳንዱን የሰውነታችንን ገጽታ በዚህ መስታወት ውስጥ እናየዋለን ፡፡