Wednesday, February 22, 2012

ኑ ቀረብ በሉ!


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/04/2004
ፍቅር የሆነ አምላካችን ምን ያህል እኛን እንዳከበረን እስቲ ለአንድ አፍታ ቆም ብልን እናስበው፡፡ አፍቃሪያችን አስቀድሞ በራሱ አርአያና አምሳል ፈጠረን ስለዚህም ክብራችን በመላእክት ዘንድ እጅግ ታላቅ ሆነ፡፡ የእግዚአብሔር መልክ አለንና እጅግ አከበሩን፡፡ ስለዚህም እርሱን እንዳገለገሉት ቆጥረው ቅዱሳን መላእክት እኛን አገለገሉን፡፡ ይህን አስመልክቶ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ አለን “እግዚአብሔር አምላክን በላይ በሰማይ የሚያገለግሉት ቅዱሳን መላእክት እኛን አገለገሉን፡፡ ይህ እግዚአብሔር አምላክ እኛን ምን ያህል እንዳከበረን የሚያሳየን ነው፡፡” ይህ በእርግጥ ድንቅ ነው፡፡
አክብሮ የፈጠረውን ሰብእናችንን በኃጢአት በማዋረዳችን ምክንያት ፈጣሪያችን ተመርሮብን ለዘለዓለም ቆርጦ አልጣለንም፡፡ ነገር ግን ፍቅሩ አገብሮት እኛን እጅግ ሊያከብረንና ሰይጣን ከማይደርስበት ከፍታ ከፍ ከፍ ሊያደርገን ሰማይና ምድርን የፈጠረ አምላክ ከድንግል ቅድስት እናታችን ማኅፀን ተወሰነ፡፡ ሥጋና ነፍስን ከእርሱዋ በመንሳትም ተወለደ፡፡ በዚህም ባሕርያችንን አምላክ አደረገው፡፡ ቅድስት እናታችንንም ሰማይ አደረጋት፡፡ አሁን እኛ ክርስቲያኖች “አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር” ስንል እነሆ እርሱዋን ሰማይ አድርገን ነው፡፡ ምክንያቱም ወልድ ባለበት አብም መንፈስ ቅዱስም አሉና፡፡ እንዲህ አድርገህ እጅግ ያከበርከንና ያፈቀርከን ፈጣሪያችን ሆይ ላንተ ምን አንደበት ነው ምስጋናን ማቅረብ የሚቻለው? 
እርሱ በዚህ ድንቅ ቸርነቱ ብቻ አላበቃም እኛንም እንደ እናቱ ለራሱ ማደሪያ በማድረግ ሰማይ አደርጎናልና እናመሰግነዋለን፡፡ እርሱ በቃሉ“ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ እርሱ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ" ”(ዮሐ.6፡56)አለን፡፡ ስለዚህም ሥጋውን ስንበላ ደሙንም ስንጠጣ ከድንግል ማኅፀን ተፀንሶ የነበረው ጌታ በእኛም ሰውነት ውስጥ ያድራል፡፡ በመሆኑም እኛም እንደ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማን ሰማዩ ሆንን፡፡ ድንግል ሆይ ራስሽን ለፈጣሪያችን ሰማይ በማድረግ እኛም ለእርሱ ሰማይ እንድንሆን ስላበቃሽን እናመሰግንሻለን፡፡ አሁን “አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር” ስንል የእኛን ሰውነት ሰማይ አድገህ የምትኖር አክባሪያችን ሆይ ስምህ ይቀደስ እያልነው ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ ቸርነትህ ምን ዐይነት ምስጋናን ማቅረብ ይቻለን ይሆን?