Monday, January 30, 2012

“ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጁዋ ከወዳጇ ጋር ያወጋችው ወግ” (ከቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
21/05/2004
ልጄ ሆይ አንተ የእኔ ስትሆን ሌሎች የእኛም ነው በማለታቸው እኔ እናትህ ቅናት አይሰማኝም ፡፡ ለአንተ ኃጢአቱን ለሚናዘዝ ሰው ሁሉ አምላኩ ሁነው ፤ አንተንም ለማገልገል ለሚተጋውም ጌታ ሁነው፤  ሁሉ የሚሹህ ልጄ ሆይ አንተን ያፈቀሩህ ሁሉ ወንድሞችህ ይሁኑ ፡፡
ልጄ ሆይ አንተ ከእኔ ማኅፀን ውስጥ በነበርክበት ወቅት እንዲሁ በውጪም በዓለም ነበርኽ፡፡ አንተ ከእኔ በሥጋ በመወለድ ከእኔ ሆድ ብትወጣም በሕቡዕ ግን ከእኔ ውስጥ ነበርህ ፡፡ኦ ! እኔን እናትህን በእጅጉ ያስገረምኽ ልጅ ሆይ አንተ ከእኔም ጋር ነህ በዓለምም ሙሉ ነህ፡፡
 ቅዱስ የሆንኽ ልጄ ሆይ በአካል የተገለጠውን አንተነትህን በሥጋዊ ዐይኖቼ  ስመለከት በነፍስ ዐይኖቼ ደግሞ  በሕቡዕ በውስጤ ያለውን ማንነትህን እስተውላለሁ፡፡ በአካል በተገለጠው ማንነትህ በኩል አዳምን ስመለከት ሕቡዕ በሆነው ማንነትህ በኩል ደግሞ ከአንተ ጋር አንድ ባሕርይ የሆነውን አባትህን እመለከታለሁ፡፡
ልጄ ሆይ! እንዲህ እጹብና ድንቅ የሆነውን ሁለት ዓይነት ገጽታዎች ያለውን ማንነትህን እኔ ብቻ ተመለከትኩትን? ልጄ ሆይ ይህን ሕቡዕ የሆነ ማንነትህን በሕብስቱ ውስጥ እንዲያዩት ፍቀድ፡፡ ሥጋህን በሚመገበው ሰው ሕሊና ውስጥ አንተነትህ ግለጥ፡፡ ልጄ ሆይ በግልጽም  ይሁን በሕቡዕ አንተነትህን  ያንተ ለሆነችው ቤተክርስቲያንህ እና ለእኔ ለእናትህ ዘወትር ግለጥልን፡፡

የአዳም ብሩካን ዐይኖች



ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
21/05/2004

ዘፍ. ም.2፡18-25 ያለው ለእኔ ልዩ አንድምታ አለው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ “ሰውን በአርያችንና በአምሳላችን እንፍጠር” አለና አዳምን ፈጠረው፡፡ በእርሱዋ ደስ ይለውም ዘንድ እጹብ ድንቅ አድርጎ ገነትን ፈጥሮ ሰጠው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር እንዲያ እጅግ ውብና ረቂቅ አድርጎ የፈጠራት ገነት አዳምን ደስ አላሰኘችውም ነበር፡፡ ለምን ቢባል አዳም በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል በመፈጠሩ የተነሣ እርሱን የሚመስል አቻ አስፈልጎት ነበርና ነው፡፡ የእርሱ አርዓያና አምሳል ያለው ደግሞ እግዚአብሔር ነው፡፡ ነገር ግን ከእርሱ ጋር እንደ አቻ ሊነጋገር አልቻለም፡፡ ምክንያቱም አዳም ፍጡር እግዚአብሔር ደግሞ ፈጣሪ ነው፤ አዳም ግዙፍ እግዚአብሔር ረቂቅ ነው፡፡ ስለዚህም ምንም እንኳ እግዚአብሔር በገጽታው አዳምን ቢመስለውም ለአዳም እንደ አቻ ወዳጅ ሊሆነው አልቻለም፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔር አርዓያ ያላት ፍጥረት አስፈለገችው፡፡
 ይህ አስቀድሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለ እውቀት ቢሆንም ሰው ቀስ በቀስ ይህንን ተረድቶ የአምላክን ሥራ እንዲያደንቅ “እግዚአብሔር ሰውን በአርዓያውና በአምሳሉ ፈጠረ፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ብሎ ወዲያው አዳምን እንደፈጠረው ሔዋንን በአካል እንድትገለጥ አላደረጋትም፡፡ ይህ ለአዳም አንዳች ትርጉም ሰጠው፡፡