Monday, January 30, 2012

የአዳም ብሩካን ዐይኖች



ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
21/05/2004

ዘፍ. ም.2፡18-25 ያለው ለእኔ ልዩ አንድምታ አለው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ “ሰውን በአርያችንና በአምሳላችን እንፍጠር” አለና አዳምን ፈጠረው፡፡ በእርሱዋ ደስ ይለውም ዘንድ እጹብ ድንቅ አድርጎ ገነትን ፈጥሮ ሰጠው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር እንዲያ እጅግ ውብና ረቂቅ አድርጎ የፈጠራት ገነት አዳምን ደስ አላሰኘችውም ነበር፡፡ ለምን ቢባል አዳም በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል በመፈጠሩ የተነሣ እርሱን የሚመስል አቻ አስፈልጎት ነበርና ነው፡፡ የእርሱ አርዓያና አምሳል ያለው ደግሞ እግዚአብሔር ነው፡፡ ነገር ግን ከእርሱ ጋር እንደ አቻ ሊነጋገር አልቻለም፡፡ ምክንያቱም አዳም ፍጡር እግዚአብሔር ደግሞ ፈጣሪ ነው፤ አዳም ግዙፍ እግዚአብሔር ረቂቅ ነው፡፡ ስለዚህም ምንም እንኳ እግዚአብሔር በገጽታው አዳምን ቢመስለውም ለአዳም እንደ አቻ ወዳጅ ሊሆነው አልቻለም፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔር አርዓያ ያላት ፍጥረት አስፈለገችው፡፡
 ይህ አስቀድሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለ እውቀት ቢሆንም ሰው ቀስ በቀስ ይህንን ተረድቶ የአምላክን ሥራ እንዲያደንቅ “እግዚአብሔር ሰውን በአርዓያውና በአምሳሉ ፈጠረ፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ብሎ ወዲያው አዳምን እንደፈጠረው ሔዋንን በአካል እንድትገለጥ አላደረጋትም፡፡ ይህ ለአዳም አንዳች ትርጉም ሰጠው፡፡
አዳም እግዚአብሔር አምላክ የእርሱን ተፈጥሮ ገንዘቡ በማድረግ እንደ ቅርብ ወዳጅ ለእርሱ በፈጠረለት ቋንቋ ሊያነጋግረው መፍቀዱን አስተዋለ፡፡ ይህ እውን ሆኖ ሊያየው በናፈቀም ጊዜ ከጎኑ አንዲት አጥንትን በመውሰድ ሴት አድርጎ ሠራት፡፡ እርሷም የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ነበራት፡፡ ስለዚህም አዳም በገነት ደስታው ሙሉ ሆነለት፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ቃል ከሴት ተወልዶ ሰው በመሆን እንዲነጋገረው ተገንዝቦአልና፡፡ ስለዚህም አባታችን አዳም ረጅም የመከራ ዘመናትን ቢያሳልፍም ዳግማዊ አዳም የተባለውን ክርስቶስን በተሰጠችው ሴት በኩል እንዲያየው ስለተረዳ ነፍሱ በሐሴት ተሞላች፡፡
አሁን እርሱ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ድንቅ የሆነው ግርማ እየተመለከተና ሲሻም ከእርሱ ጋር እየተነጋገረ ፍጹም ሙሉ በሆነ ደስታ ውስጥ ይኖራል፡፡ ቅዱሳንም እንደርሱ ክርስቶስን ገነት አድርገው ይኖሩ ዘንድ ተጠሩ፤ ብዙዎች አርአያቸው የሆነውን ክርስቶስን እያዩ ከእርሱ ፍቅር ተመገቡ፡፡ እኛም ለዚህ ክብር ተጠራን፡፡
 ኑ የሴት ልጅን ልዩ የሆነ ድንቅ ተፈጥሮ እናድንቅ! ይህች ተፈጥሮ ፍቅር ለሆነው ክርስቶስ እናቱ ሆነች፣ እልፍ አእላፋት መላእክት ከተሙባት፤ ፍጹም ሰማያዊ የሆነ ዝማሬን አቀረቡባት፡፡ ከገነት የሚልቀው የሴት ልጅ ተፈጥሮ እንዴት ድንቅ ነው! አዳም ረቂቅ ምሥጢር ያላትን የሴትን ተፈጥሮ አስተዋሎ እጅግ ወደዳት፣ አከበራትም፤ በእርሱዋም አምላኩን አመሰገነ፡፡ ምንም እንኳ በእርሱዋ ምክንያት ለጽኑ መከራ ተላልፎ የተሰጠ ቢሆንም አልተመረረባትም፤ የነቀፋ ስምም አላወጣባትም፤ እንዳውም ከስሞች ሁሉ በላይ የሆነ ስምን ሰጣት፡፡ ሔዋን አላት፤ ትርጓሜውም የሕያዋን ሁሉ እናት ማለት ነው፡፡ ይህ ስም ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ “በሔዋን ምትክ የሕያዋን ሁሉ እናት ይሆን ዘንድ ክርስቶስ በመስቀሉ ጥምቀትን መሠረተልን … እርሱም ከውኃና ከደሙ መንፈሳዊ በሆነ መልኩ ልጆችን ወለደ” በማለት ለክርስቶስ ሰጥቶት እናገኘዋለን፡፡ በእርግጥም ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ ተጠምቀን ከጎኑም በፈሰሰው ደሙ ተዋጅተን ከክርስቶስ ተወልደናል፡፡
 በእውን እኛ አዳማውያን የአባታችን የአዳም ዐይኖች አሉንን? እንደ እርሱ ለሴት ልጅ ተፈጥሮ ልዩ አክብሮትና ቦታ አለንን? ብዙዎቻችን ቅዱሳን ባልኖሩበት፣ በአይሁድ ልማድ ሴት ልጅን አሳንሰን የምንመለከትና እንደ እቃና መገልገያ እንዲሁም ማሻሻጫ በሚቆጥሩ ምዕራባዊያን አስተሳሰብ የጠፋን አይደለንምን? የአዳም ዐይኖች እንዴት ግሩማን ነበሩ! እኛም ብዙ አጠፋን እግዚአብሔር ያከበረውን ተፈጥሮ በደልን፣ አሳዘንን፣ ናቅነው፣ አቃለልነውም፡፡ ከእንግዲህ ግን ላይደገም አምላክ ለአዳም አባታችን የሰጠውን ማስተዋል ለእኛም ይስጠን፤ ላለፈውም ይቅር ይበለን ከሚመጣውም ይጠብቀን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡  

No comments:

Post a Comment