ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
21/05/2004
ልጄ ሆይ አንተ የእኔ ስትሆን ሌሎች
የእኛም ነው በማለታቸው እኔ እናትህ ቅናት አይሰማኝም ፡፡ ለአንተ ኃጢአቱን ለሚናዘዝ ሰው ሁሉ አምላኩ ሁነው ፤ አንተንም ለማገልገል
ለሚተጋውም ጌታ ሁነው፤ ሁሉ የሚሹህ ልጄ ሆይ አንተን ያፈቀሩህ ሁሉ
ወንድሞችህ ይሁኑ ፡፡
ልጄ ሆይ አንተ ከእኔ ማኅፀን ውስጥ በነበርክበት
ወቅት እንዲሁ በውጪም በዓለም ነበርኽ፡፡ አንተ ከእኔ በሥጋ በመወለድ ከእኔ ሆድ ብትወጣም በሕቡዕ ግን ከእኔ ውስጥ ነበርህ ፡፡ኦ
! እኔን እናትህን በእጅጉ ያስገረምኽ ልጅ ሆይ አንተ ከእኔም ጋር ነህ በዓለምም ሙሉ ነህ፡፡
ቅዱስ የሆንኽ ልጄ ሆይ በአካል የተገለጠውን አንተነትህን በሥጋዊ ዐይኖቼ ስመለከት በነፍስ ዐይኖቼ ደግሞ በሕቡዕ በውስጤ ያለውን ማንነትህን እስተውላለሁ፡፡ በአካል በተገለጠው ማንነትህ
በኩል አዳምን ስመለከት ሕቡዕ በሆነው ማንነትህ በኩል ደግሞ ከአንተ ጋር አንድ ባሕርይ የሆነውን አባትህን እመለከታለሁ፡፡
ልጄ ሆይ! እንዲህ እጹብና ድንቅ
የሆነውን ሁለት ዓይነት ገጽታዎች ያለውን
ማንነትህን እኔ ብቻ ተመለከትኩትን? ልጄ ሆይ ይህን ሕቡዕ የሆነ ማንነትህን በሕብስቱ ውስጥ እንዲያዩት
ፍቀድ፡፡ ሥጋህን በሚመገበው ሰው ሕሊና ውስጥ አንተነትህ ግለጥ፡፡ ልጄ ሆይ በግልጽም ይሁን በሕቡዕ አንተነትህን ያንተ ለሆነችው ቤተክርስቲያንህ እና ለእኔ ለእናትህ ዘወትር ግለጥልን፡፡
ልጄ ሆይ ሥጋህ ከሆነውን ሰማያዊ ሕብስትህ መመገብን የሚጠሉ የአንተን
ሰው መሆን የሚጠሉ ናቸው፡፡ ከዚህ ሕብስት ይመገብ ዘንድ ፈቃዱ የሌለው ሰው ከአንተ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡ ስለኛ ስለተቀበልከው
መከራ ምስክር ከሆነው ቅዱስ ሥጋህና ክቡር ደምህ ሊመገብ የወደደ እርሱ እነሆ ያንተ የአካል ክፍል ሆነ፡፡
ነገር ግን ጌታ ሆይ ቅዱስ ሥጋህና ክቡር ደምህ አንተን እንድናቅ አደረገን፡፡
ኢአማንያን ግን ከዚህ ክቡር ምሥጢር ተካፋይ ባለመሆናቸው አንተ ከማወቅ ራቁ፡፡ አካልህን ባንተ ያላመኑትም ተመልክተውታል፤ ሕያው የሆነውን ቅዱስ ሥጋህና ክቡር ደምህን ግን በአንተ ያላመኑት ለመመገብ
አልታደሉም፡፡ በዚህም ምክንያት በአንተ ያላመኑት አንተን ለመረዳት በእጅጉ የራቁ ሆኑ ፤ እድል ፈንታቸውም ጽኑ ጨለማና ስቃይ ሆነ፡፡
እነሆ ክቡር ደምህ ከቅዱስ ሥጋህ ጋር በተዋሕዶ አለ፡፡
እርሱን ለተመገበው በፍቅር ጣትነት በእምነት ሕብረ ቀለማት በሕቡዕ በልብ ጽላት ላይ መንፈስ ቅዱስ ሕግጋቱን ይጽፍለታል፡፡ ጌታ ሆይ
እውነተኛ የሆነውን ይህን ሥጋህን በመመገቡ ምክንያት በልቡ ውስጥ ተቀርፆ የነበረውን የጣዖት ምስል የተወገደለት ሰው ልጄ ሆይ እርሱ
ብፁዕ ሰው ነው ፡፡
ልጄ ሆይ አንተ ሕፃናትን ለማባበል ሲባል የሚቀርበው መዝሙር የሚቀርብልህ
ሕፃን አይደለህም፡፡ የአንተ ፅንሰት እጅግ ልዩ ነው ልደትህም ድንቅ ነው፡፡ ስለዚህም በመንፈስ ቅዱስ እገዛ ካልሆነ በቀር ለአንተ
የሚገባ ዝማሬን ሊያቀርብልህ የሚችል ሰው ማን ነው ? አንተን በተመለከተ አዲስ የሆነ ቅኔ በውስጤ በዝምታ ይመላለሳል ፡፡
ከእኛ ዘንድ እንግዳ የሆንኸ የሰው ልጅ ሆይ አንተን ማን ብዬ ልጥራህ
? ልጄ ብዬ ልጥራህን ?ወይስ ወንድሜ ? ሙሽራዬስ ብዬ ? ወይስ
ጌታዬ ብዬ ልጥራህ?
ልጄ ሆይ እኔ እናትህ ለአንተ በሥጋ አባት ከሆነው ከዳዊት ወገን የሆንኹ እኅትህ ነኝ ፡፡ እኔ የአንተ እናት ነኝ ምክንያቱም
በሥጋ ፀንሼህ ወልጄሃለሁና፤ አንዲሁ እኔ ለአንተ የታጨሁ ሙሽሪትም የተባልኩት ነኝ ፤ ምክንያቱም ለአንተ ተቀድሼ ተጠብቄአለሁና
፡፡ እንዲሁ እኔ ያንተ ልጅም ነኝ ምክንያቱም ከእኔ የነሣኸውን ሰውነት መልሰህ አልብሰኸኛልና፡፡
የእግዚአብሔር አንድያ ልጁ ከላይ ከልዕልናው ዝቅ በማለት በእኔ ዘንድ
ማደሪያውን አደረገ፡፡ እርሱን በሥጋ ፀንሼ በመውለዴም እናቱ ሆንኹ
፡፡ እርሱ በሁለተኛ ልደቱ ከእኔ ዘንድ በሥጋ ሲወለድ ፣ እኔም በሁለተኛ
ልደት ከእርሱ ዘንድ ተወለድኹ ፡፡ በዚህም እርሱ የእኔን የእናቱን
ሥጋ ሲለብስ እኔም ከእኔ የነሣውን ክቡር የሆነውን ሥጋውን ለበስኹ፡፡
የምድር አበባ የተባለችው ትንሹዋ አበባ በቆላው አበባ(በክርስቶስ)
መዓዛ ምክንያት ተማርካ ነፍስም አልቀረላት ፡፡ የሽቱ ቅመማ ቅመማት ግምጃ ቤት የሆነው እርሱ መዓዛውን ለማግኘት አበባ ወይም መዓዛው
እጅግ ማራኪ እንዲሆን ሌላ መዓዛ አላስፈለገውም እንዲሁም በሥጋ ተፀንሶ እንዲወለድ የወንድ ፈቃድ አላስፈለገውም፡፡ ምክንያቱም ፀንሰቱ የሚከናወነው በመንፈስ ቅዱስ ግብር ነውና፡፡
ለሚስት ባሏ ራሱዋ ነውና እርሱን ታገለግለዋለች፡፡ ነገር ግን ጌታ ሆይ በአንተ የተነሣ ያንተ ታቦት ሆኜ በመገኘቴ ካህናት
አገለገሉኝ፡፡
ሙሴ እግዚአብሔር በእጆቹ የጻፈባቸውን ሁለቱን ፅላቶች ተሸከማቸው ፤
ዮሴፍም ፍጥረታትን ያስገኘው ጌታ በተዋሕዶም ጽላቱ ያደረገውን አካል በእቅፉ ተሸከመው፡፡ .... ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ
ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
Kale hiwot yasemaln edmina tina yisth Egziabher betam etsub dink tsuhuf new...
ReplyDelete