Saturday, May 25, 2013

አቤቱ ይህን አትንሣን!!!



17/09/2005
በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ሰው የሚድነው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው “በጸጋ ድናችኋልና” እንዲል፡፡ ክርስቶስ ዘለዓለማዊውን ጸጋውን ከሰጠን ቆየ ክርስትናም በክርስቶስ ከተመሠረተች እጅግ ቆየች ግን አሁንም ያው ነች ሰማያዊት ናትና የዘመን ቁጥር የላትም ሁሌም አዲስ ናት፡፡ ሰዎችን ዘመን ከማይቆጠርባት ሰማያዊት ሀገር ታፈልሳለች በዚያም ሰማያውያን ቅዱሳን መላእክትና ቅዱሳን ነፍሳት ከትመዋል፡፡ ሰው ልቡናው ከበራ የሚኖርባትን ዘመን የማይቆጠርላትን ሰማያዊቱን ዓለም ይረዳታል ጣዕሙዋንም ይቀምሳል፡፡ ጣዕሟን ማንም በቃላት ሊገልጣት አይችልም፡፡ ለዚህ ዓለም ቋንቋ ባዕድ ናት ሕይወቱዋም ልዩ ነው፡፡ ይህችን ጣዕም እየቀመሱ መኖር እንዴት መታደል ነው!!! ቢሆንም የሚወደን አምላክ እርሱዋን አልነሣንም ግቡም ይህ ነው የዚህች ሰማያዊት ስፍራን ጣዕም በሁለመናችን እንረዳትና በእርሱዋ ውስጥ ለዘለዓለም እንድንኖር ነው፡፡ ጌታ ሆይ ከዚህች ሥፍራ በመንፈስ እንዳንወጣ ሁሌም የዚህችን ሰማያዊት ሥፍራ እያጣጣምን እንድንኖር እርዳን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡ 

የትኛውን በግ ኖት?


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
17/09/2004


አቤል ቅን ሰው ነበር፤ ነገር ግን እንደ በግ ወደ ዱር በገዛ ወንድሙ ቃየን ተነድቶ ተገደለ፡፡ እንደ አቤል በቃየል የተገደሉ ብዙ ወገኖች አሉን፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን እንደ ቀድሞው አቤል መሆን የሚያዋጣ አይደለም፡፡ በአሁኑ ቃየኖች የሚገደሉ አቤሎች ሞታቸው የነፍስ ሞት ነው፡፡ ቃሉም የሚነግረን አሰናካዩም ተሰናካዩም አብረው እንደሚጠፉ ነው፡፡ በግ እንድንሆን የተጠራን ቢሆንም የትኛውን የበግ ዐይነት መሆን እንደሚገባን ግን ልንለይ ይገባናል፡፡ ሁለት ዓይነት በጎች አሉ፡፡ አንደኞቹ በጎች በእውነት ክርስቶስን የመሰሉ በቀኝ የሚቆሙት ቅዱሳን ናቸው፡፡ እነዚህ በየትም አቅጣጫ እንደቀድሞው አቤል ላታላችሁ ብትሉ አይሳካላችሁም፡፡ ምክንያቱም እነርሱ የሚመሩት በመንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡ መንፈሳዊውን ሰው ፍጥረታዊው ሰው ሊመረምረው አይችልም፡፡ ፍጥረታዊው ሰው መንፈሳዊው መረዳት የለውም፡፡ መንፈሳዊው ግን ፍጥረታዊውን ያውቀዋል ይመረምረዋል፡፡ እናም የፍጥረታዊውን የቃየንን አመለካከት የሐዲስ ኪዳኑ አቤል፣ ጌታን የለበሰው ከጻድቃን ሕብረት ያለው በግ ፈጥኖ ይረዳዋል፡፡ ነገር ግን እንደው የጥፋትም በጎች አሉ፡፡ ለእነርሱ ልቤ ያዝናል፡፡ ዳዊት ስለእነርሱ
“ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ፡፡ ይህች መንገዳቸው መሰናክላቸው ናት ከእነርሱም በኋላ የሚመጡ በአፋቸው እሺ ይላሉ፡፡ እንደ በጎች ወደ ሲኦል የሚሄዱ ናቸው እረኛቸው ሞት ነው፡፡”(መዝ.48፡12-14) ይላቸዋል፡፡ እነዚህ በጎች ያሳዝኑኛል፡፡ ለነፍሳቸው እረኛው ሞት ነው፤ ሞትም በቁማቸው ይገድላቸዋል፡፡ መሞታቸውን ግን አይረዱትም እነዚህ እንደ ቀድሞውም አቤል በነፍሳቸው ያልተጠቀሙ ከአዲሶችም አቤሎች ኅብረት የሌላቸው እንደው ሞት የነጋራቸውን ሁሉ አሜን ብለው የሚቀበሉ ናቸው፡፡ አቤቱ ሰውን ሁሉ ሞት ወደ ሲኦል የሚመራው በግ አታድርገው፡፡ ይልቅ አንተን መስለው ሰይጣንን ወደ ሲኦል የሚነዱ አድርጋቸው እንጂ፡፡