Monday, March 16, 2015

ክርስትና

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 

06/07/2007

ክርስትና ሰው ሆነን የተፈጠርንበትን ድንቅና ግሩም የሆነውን እግዚአብሔርን የምንመስልበት አቅምን የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስን በኃጢአታችን ምክንያት አጥተን ስንባዝን ለነበርነው ክርስቶስ በመስቀሉ ዳግም የሰጠን እውቀት ሳይሆን ሕይወት ነው። ሲጠቃለል ክርስትና ማለት ሰው መሆን ማለት ነው። ሰውን ሰው የሚያሰኙት ተፈጥሮውና ተግባሩ ናቸው። ተፈጥሮው ሲባል ሰው ግሩምና ድንቅ የሆነውን እግዚአብሔርን የሚመስልበት አቅሙን ማለታችን ነው። እግዚአብሔርን የሚመስልበት አቅሙን ግን ወደ ተግባር መልሶ ይሠራበት ዘንድ ግን መምህር የሚሆነው መንፈስ ቅዱስ በውስጡ ያድርበት ዘንድ ግድ ነውና ጌታችን አዳምን ከምድር አፈር ካበጀው በኋላ የሕይወት እስትንፋስን በአፍንጫው እፍ በማለት ሰውነቱን ምድርን በውበት ላስጌጣት መንፈስ ቅዱስ ማደሪያ አደረጋት። ሰው ለዚህ በውስጡ ላደረበት መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሲታዘዝ ሰው ተብሎ ወደ መጠራት ይመጣል። ሰው ከሆነ ደግሞ ክርስቲያን ሆነ ማለት ነው። ክርስትና እንግዲህ እንዲህ ናት ወሬ ሳትሆን ሕይወት ናት። ክርስትና ሰው በመሆን ሰው የመሆንን ትርጉም ያሳየንን ክርስቶስን መምሰልን የምትጠይቅ ናት። አቤቱ አምላኬ ሆይ እባክህ ግሩምና ድንቅ ወደሆነው ሰዋዊው ማንነቴ በቃል ሳይሆን በተግባር አድግ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ለነፍሴ እውቀትና ሕይወት እንዲሁም ብርሃን ሆኖ አንተን እመስል ዘንድ እርዳኝ።  የቀደመውን ኃጢአቴን አታስብብኝ ከኃጢአት ፈቃድም ንጹሕ አድርገኝ። ልቡናዬን ለፍጥረት ሕይወት በሆነው ሕያው ቃልህ ሙላው ። አሜን ለዘለዓለም ይሁን ይደረግልኝ።

አራቱ ልደታት

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 

06/07/2007

የክርስቲያን አፈጣጠሩና እድገቱ እጅግ ግሩም ነው። ልደቱ ፍጥረታዊና መንፈሳዊ ብለን ለሁለት ከፍለናቸው ልንመለከታቸው ብንችልም ሁለትም ሦስትም  መንፈሳዊ ልደታት አሉት። ሁሉም ግን መሠረታዊያን ናቸው።
ሰው ከእናትና ከአባቱ አስቀድሞ ሳይፈጠር መንፈሳዊው ልደት ሊፈጸምለት አይችልም። ስለዚህ ፍቅር በሆነው አምላክ በሥጋ ሰው ሆኖ ሊፈጠር ይገባዋል። ይህ ልደት ግን በቂ ነው አይባልም። ሌላ አባ አባ የሚልበትን ልደት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ በስመ ሥላሴ ሊወለድ ይገባዋል።
ይህም በራሱ ሙሉ አያደርገውምና አዲስ ለተፈጠረበት ተፈጥሮ ክርስቶስን ወደመምሰል ማደግ ይጠበቅበታል። ይህ ክርስቶስን የመምሰል ደረጃ ሦስተኛ ልደት ይባላል። ይህም ክርስቶስን በተግባር ወደ  መምሰል የመምጣት ሂደት ነው። ወደዚህ መንፈሳዊ ከፍታ  የደረሰ ሰው ላይ ክርስቶስ በእርሱ ይገለጣል።  ሰዎች ሁሉ የክርስቶስን መልክ በእርሱ ላይ ይመለከታሉ። ነገር ግን ደግሞ ሌላ አራተኛ ልደት ያስፈልገዋል። እርሱም በትንሣኤ ለድል አድራጊዎቹ ከክርስቶስ የሚሰጥ ልዩና ዘለዓለማዊ ስጦታ ነው። ክርስቶስ በትንሣኤ ሥጋችንን እንደ ራሱ ሥጋ አድርጎ በመለወጥ ልክ በደብረ ታቦር ወደ አሳየን ክብሩ በማሸጋገር የምንወለድበት ልደት ነው። ይህን ዓይነት ልደትን በምሳሌነት አስቀድሞ በሙሴ አሳይቶን ነበር። እውነተኛውን ልደት ግን በትንሣኤ የእርሱን ሥጋ እንዲመስል አድርጎ ሥጋችንን በመለወጥ ይሰጠናል። ይህን አስመልክቶ ጌታችን በቃሉ "እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።"(ማቴ.19:28) ብሎናል። በእውነት እርሱ ለዚህ ክብር የፈጠረን ጌታ ፍቅር የሆነውን ሰውነቱን ለብሰን ለዘለዓለም ስናመሰግነው እንድኖር ያብቃን። ለዘለዓለም አሜን።

መዝሙር 89 በቅዱስ ጀሮም

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
06/07/2007

በመዝሙሩ መግቢያ ላይ የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ጸሎት የሚል ተጽፎ እናገኛለን፡፡  .....
“አቤቱ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆነህልን” ብሎ መዝሙረኛው መዝሙሩን ይጀመራል፡፡ መጠጊያ የሚፈልግ ሰው ከሚግለበለብ እሳት ወይም ወላፈን ወይም ከክፉ አውሬ ወይም ነፍሱን ከሚፈላለጋት ጠላቱ ከሚታደገው ዘንድ ነው መጠጊያውን የሚያደርገው፡፡ እኛም እንዲሁ ከዚህ ዓለም የኃጢአት እሳትና ወላፈን ወይም ደግሞ እኛን ከሚያድነን  አውሬ ዲያብሎስ  ያደነን ዘንድ “የምትገዛልህን ነፍስ ለአራዊት አትስጣት የችግረኞችህን ነፍስ ለዘወትር አትርሳ”(መዝ.73፡19) እያልን ወደ መጠጊያችን እግዚአብሔር  ዘወትር እናንጋጥጣለን፡፡ ጠላቶቻችን በእኛ ላይ በርትተውብናልና በክንፎችህ ጥላ ሰውረን ብለን እንማጸነዋለን ምክንያቱም እርሱ መጠጊያችን ነውና፡፡