በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
06/07/2007
ክርስትና ሰው ሆነን የተፈጠርንበትን ድንቅና ግሩም የሆነውን እግዚአብሔርን የምንመስልበት አቅምን የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስን በኃጢአታችን ምክንያት አጥተን ስንባዝን ለነበርነው ክርስቶስ በመስቀሉ ዳግም የሰጠን እውቀት ሳይሆን ሕይወት ነው። ሲጠቃለል ክርስትና ማለት ሰው መሆን ማለት ነው። ሰውን ሰው የሚያሰኙት ተፈጥሮውና ተግባሩ ናቸው። ተፈጥሮው ሲባል ሰው ግሩምና ድንቅ የሆነውን እግዚአብሔርን የሚመስልበት አቅሙን ማለታችን ነው። እግዚአብሔርን የሚመስልበት አቅሙን ግን ወደ ተግባር መልሶ ይሠራበት ዘንድ ግን መምህር የሚሆነው መንፈስ ቅዱስ በውስጡ ያድርበት ዘንድ ግድ ነውና ጌታችን አዳምን ከምድር አፈር ካበጀው በኋላ የሕይወት እስትንፋስን በአፍንጫው እፍ በማለት ሰውነቱን ምድርን በውበት ላስጌጣት መንፈስ ቅዱስ ማደሪያ አደረጋት። ሰው ለዚህ በውስጡ ላደረበት መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሲታዘዝ ሰው ተብሎ ወደ መጠራት ይመጣል። ሰው ከሆነ ደግሞ ክርስቲያን ሆነ ማለት ነው። ክርስትና እንግዲህ እንዲህ ናት ወሬ ሳትሆን ሕይወት ናት። ክርስትና ሰው በመሆን ሰው የመሆንን ትርጉም ያሳየንን ክርስቶስን መምሰልን የምትጠይቅ ናት። አቤቱ አምላኬ ሆይ እባክህ ግሩምና ድንቅ ወደሆነው ሰዋዊው ማንነቴ በቃል ሳይሆን በተግባር አድግ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ለነፍሴ እውቀትና ሕይወት እንዲሁም ብርሃን ሆኖ አንተን እመስል ዘንድ እርዳኝ። የቀደመውን ኃጢአቴን አታስብብኝ ከኃጢአት ፈቃድም ንጹሕ አድርገኝ። ልቡናዬን ለፍጥረት ሕይወት በሆነው ሕያው ቃልህ ሙላው ። አሜን ለዘለዓለም ይሁን ይደረግልኝ።
No comments:
Post a Comment