Tuesday, August 7, 2012

የቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
2/12/2004
(1996 ዓ.ም ለሰንበት ትምህርት ቤት ማስተማሪያ የተዘጋጀ)
መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባቶች ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግል እንደሆነች አስረግጠው ይስተምራሉ፡፡ እርሱዋ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናት ፤ ሃሳቡዋም ሰውነቱዋን ለእግዚአብሔር አምላኩዋ ቀድሳ በድንግል መኖር ነበር፡፡ ይህን ከንግግሩዋ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለቅድስት ድንግል ማርያም “ ደስ ይበልሽ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፡፡… ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋን አግኝተሻልና አትፍሪ እነሆ ትጸንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ…” ባላት ጊዜ የሷ መልስ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል” ነበር፡፡/ሉቃ. 1፥27-36/ ይህም በድንግልና ለመኖር እንደ ቆረጠች ያስረዳናል፡፡ አግብታ ልጅ የመውለድ ፈቃዱ ቢኖራት ኖሮ መልአኩን ከማን? ብላ በጠየቀችው ነበር፡፡ በተጨማሪም ወንድ ስለማላውቅ ማለቷ ወደፊትም ወንድ ባለማወቅ በድንግልና ለመኖር ለእግዚአብሔር ስለተሳልኩ እንዴት ይሆናል? ማለቷ ነበር፡፡