Monday, January 23, 2012

ከሕግ በላይ የሆነው የደስታና የነጻነት ሥፍራ (ጋብቻ)



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/05/2004
  ድሮ ድሮ ያኔ በገነት አንድ ሔዋን የምትባል ሴት ነበረች፤ እርሱዋም ዓለሙዋ በሆነ በአዳም ሰውነት ውስጥ ትኖር ነበር፡፡  አንድ ወቅት ባልዋ አዳም በውስጡ እየተመላለሰች ደስ ታሰኘው የነበረችውን ይህቺን ሴት በአካል ተገለጣ ሊያያት ፈለገ፡፡ ነገር ግን በውስጡ ተሰውራለችና ሊያያት አልተቻለውም፡፡ ስለዚህም የደስታ መፍሰሻ በሆነችው ገነት እጅግ ታላቅ በሆነ ትካዜ ተዋጠ ተከዘ አዘነ፡፡ ገነትም ገነት አልመሰለችውም፡፡ ነገር ግን ልብ ያሰበውን ኩላሊት ያመላለሰውን የሚያውቅ እግዚአብሔር የአዳምን ጽኑ ኀዘን ተመለከተ፡፡ ስለዚህም ጽኑ እንቅልፍ በእርሱ ላይ ጣለበት፡፡ ይህንን ቅዱሳን አባቶች በተለይ አምብሮስ ተመስጦ ይለዋል፡፡ በዚያ ጊዜ ነፍስ በሥጋ ሰውነቱዋ ላይ እግዚአብሔር የሚያከናውነውን ትመለከት ዘንድ ወደ አምላኩዋ ተነጠቀች፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከሥጋዋ ከግራ ጎኑ፣ ከልቧ አጠገብ ሔዋንን  ለይቶ ገለጣት፡፡