Monday, January 23, 2012

ከሕግ በላይ የሆነው የደስታና የነጻነት ሥፍራ (ጋብቻ)



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/05/2004
  ድሮ ድሮ ያኔ በገነት አንድ ሔዋን የምትባል ሴት ነበረች፤ እርሱዋም ዓለሙዋ በሆነ በአዳም ሰውነት ውስጥ ትኖር ነበር፡፡  አንድ ወቅት ባልዋ አዳም በውስጡ እየተመላለሰች ደስ ታሰኘው የነበረችውን ይህቺን ሴት በአካል ተገለጣ ሊያያት ፈለገ፡፡ ነገር ግን በውስጡ ተሰውራለችና ሊያያት አልተቻለውም፡፡ ስለዚህም የደስታ መፍሰሻ በሆነችው ገነት እጅግ ታላቅ በሆነ ትካዜ ተዋጠ ተከዘ አዘነ፡፡ ገነትም ገነት አልመሰለችውም፡፡ ነገር ግን ልብ ያሰበውን ኩላሊት ያመላለሰውን የሚያውቅ እግዚአብሔር የአዳምን ጽኑ ኀዘን ተመለከተ፡፡ ስለዚህም ጽኑ እንቅልፍ በእርሱ ላይ ጣለበት፡፡ ይህንን ቅዱሳን አባቶች በተለይ አምብሮስ ተመስጦ ይለዋል፡፡ በዚያ ጊዜ ነፍስ በሥጋ ሰውነቱዋ ላይ እግዚአብሔር የሚያከናውነውን ትመለከት ዘንድ ወደ አምላኩዋ ተነጠቀች፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከሥጋዋ ከግራ ጎኑ፣ ከልቧ አጠገብ ሔዋንን  ለይቶ ገለጣት፡፡




በመቀጠልም ትዕይንቱን ትመለከት የነበረችውን የአዳምን ነፍስ ከሥጋዋ ጋር እንድትዋሐድ በማድረግ በእግዚአብሔር ቅዱስ እጆች የተሠራችውን ሔዋንን በሥጋዊም ዐይኖቿ እንድትመለከታት አደረጋት፡፡ አዳምም ናፍቆቱን እግዚአብሔር አምላኩ ፈጽሞለታልና እጅግ ደስ ተሰኘ፡፡ አካሉን ዓለም አድርጋ ትኖር የነበረችውን ደስታውና አክሊሉ የሆነችውን ሔዋንን በነፍሱም በሥጋውም ተመልክቶአታታልና ከሃዘኑ ተጽናና፡፡ ወደ ፊትም ከእኔ ተነጥላ ትኖር ዘንድ አልሻምና ጌታ ሆይ ዓለሙዋ ወደ ሆነው ሰውነቴ ገብታ ትኖር ዘንድ ፍቀድ ብሎ እግዚአብሔር አምላክን ተለማመነው፡፡ ስለዚህም ስሙዋ ከእንግዲህ ሴት ትባል አለ፡፡ መልእክቱም ጌታውን ከአጥንቴ አጥንት ከሥጋዬ ሥጋ ናትና ሚስቴ ትሁነኝ ብሎ ሲጠይቀው ነበር፡፡ ስለዚህም  እግዚአብሔር አምላክ "ሰው እናትና አባቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ፡፡ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ"  ብሎ ባልና ሚስት በማድረግ አንድ ሥጋ አንድ አጥንት አደረጋቸው፡፡
ይህ ተዋሕዶ በክርስቶስና በቤተክርቲያን መካከል የተደረገውን ተዋሕዶ ይመስላል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች በጥምቀት የክርስቶስን አካል ዓለም አድርገን እንኖራለን ፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ኤፍሬም ምን እንደሚል ስሙ “ጌታ ሆይ የሰውነት ክፍሎችህን ዓለም አድርጌ ተመላለስኹባቸው፡፡ በእነርሱም ውስጥ ሁሉንም ዓይነት ጸጋዎችን አገኛለሁባቸው፡፡ መልአኩ የምትገለባበጥ ሰይፍን ይዞ ወደሚጠብቃት ገነት በጦር በተወጋው ጎንህ በኩል ገባሁኝ” አለ፡፡ ይህ እኮ ድንቅ የሆነ ምሥጢር ነው!! እስቲ እናስተውለው ሔዋን ከአዳም ጎን ተገኘች፡፡ እኛም ከአፍቃሪያችን ጎን በፈሰሰው ውኃና ደም ተገኘን፡፡ ሔዋን አስቀድማ በአዳም ሰውነት ውስጥ ነበረች፤ ነገር ግን አልተገለጠችም ነበር፡፡ እኛም በተፈጥሮአዊው ልደት ተወልደን በሕይወት ነበርን፡፡ ግን መንፈሳዊ ልደቱ አልተፈጸመልንም ነበር፡፡ እንዲያ ካልሆነ የትኛው አካላችን ነው ከገቦው በፈሰሰው ውኃ ተጠመቆ ሊወለድ የሚችለው? ቅዱስ ጳውሎስም ይህ አስመልክቶ ሲናገር “አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም”ብሎናል፡፡(1ቆሮ.15፡46) ነገር ግን እንዲህ ሲባል ከክርስቶስ ጋር አስቀድመን ነበርን ማለቴ ግን አይደለም፡፡ ነገር ግን ከጥምቀት በፊት አካላችን ነበረ ስል ነው፡፡ ይህ ምሥጢር በእውነት ድንቅ ነው፡፡
በዚያ ሔዋን አስቀድማ የአዳምን ሰውነት ዓለሙዋ አድርጋ እንደኖረች፤ የተሻለና የሚመረጥ ነውና እኛም ክርስቲያኖች የዳግማዊ አዳምን የክርስቶስን ሰውነት ዓለም አድርገን እንድንኖር በጥምቀት ተወለድን፡፡ ስለዚህ አዳም ለሔዋን ዓለሙዋ ሲሆን፡፡ ሔዋን ደግሞ ለአዳም ማረፊያው ቤቱ ወይም ገነቱ ናት፡፡ ነገር ግን ለአዳምና ለሔዋን የተሠራው ያ የጥንቱ ሥርዐት አሁንም ያው ነው አልተቀየረም፡፡ ስለዚህም ሴት ልጅ በባሉዋ ላይ እንደ ልቡዋ ብትዛና ምን ነውር አለበት? ለባልየው “ከጉብዝናህም ሚስት ጋር ደስ ይበልህ፡፡ እንደ ተወደደች ዋላ እንደ ተዋበችም ሚዳቋ ጡትዋ ሁል ጊዜ ታርካህ በፍቅሩዋም ሁልጊዜ ጥገብ፡፡”(ምሳ.18፣19) የተባለለት ከሆነ ለሚስት ስለምን ይህ ይከለከላል? እንዳውም“ባሎች ሆይ ክርስቶስ ደግሞ ቤተክርስቲያንን እንደወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ” እንዲል ፍቅርን መስጠት ከባል አብዝቶ ይጠበቃል፤ ምክንያቱም አንድ ቅዱስ "ሚስት የሌለው ሰው ቤት እንደሌለው ሰው ነው" እንዲል በእርሱዋ አርፎአልና እርሱ ደስ እንደተሰኘ እርሱዋንም ደስ ሊያሰኛት ይገባዋል፡፡(ኤፌ.5፡25፣26)
 ሴት ልጅ ከባሉዋ ጋር ባለት ግንኙነት ሕግ ሊገድባት አይገባትም ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደ ሕፃን እየቦረቀች ከውድ ባለቤቱዋ ጋር ብትኖር አግባብነት አለው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሴትን ልጅ በምድር ባኖራት ዘመን ሁሉ በነጻነት ትኖርበት ዘንድ የሰጣት ግዛቱዋ ባልዋ ነው፡፡ እርሱ ላይ እንደፈቀደች እንዳትሆን ልትከለከል አይገባትም ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ ፤ አይተፋፈሩም ነበር ፡፡”(ዘፍ.2፡25) እንዲሁም “ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ይላልና አንድ ሥጋ ከሆኑ እንዴት ሊተፋፈሩ ይችላሉ? ስለዚህም ለባል ሚስቱ የደስታ መፍሰሻ ገነቱ ናትና በእርሱዋ ደስ ይበለው፤ ሚስትም እርሱዋ የተገኘችበት ዓለሙዋ ነውና በባልዋ ደስ ይበላት፡፡ ምክንያቱም ትዳር ማንም ጣልቃ የማይገባበት የባልና የሚስት ግዛት ነውና፡፡ አምላክ የተጋቢዎችን ሰርግ ይባርክ ቤታቸውንም በፍቅር ይሙላ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡   




    

3 comments:

  1. kale hiwot yasemalin wedmachin bewnetu betam emyastemru tsihufochn new emttsifew, tsegawn yabzalh amlake selam .

    ReplyDelete
  2. kale hiwot yasemalin berta wede fit

    ReplyDelete
  3. wendima Egiziabihari tsegawin yabizalihi bkibiri befikiri yitebikihi

    ReplyDelete