Tuesday, January 24, 2012

“ታላቅ ምልክት በሰማይ ታየ”(ራእ.12፡1)



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
16/05/2004
እነሆ ታላቅ የሆነ ለሰዎች ልጆች መዳን የሚጠቅመውና ትርጉም ያለው በአምላክ የተፈጸመው ታላቁ  ምልክት የታየው በምድር ላይ እንጂ በሰማያት ከመላእክት ጉባኤ አይደለም፡፡ እርሱ ራሱ በነቢዩ “ጌታ ራሱ ምልክትን ይሰጣቸኋል እነሆ ድንግል ትፀንሳለችው ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች”(ኢሳ.7፡14) እንዲል ታላቅ የሆነው ምልክት የታየው በምድር ነው፡፡ ሰማያውያን መላእክት ራሳቸው እንኳ ይህ ታላቅ የሆነ ምልክት ለማየት ሲሉ ጌታ ከተወለደበት ግርገግም ተገኙ፤ "ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ" እያሉ በምድር ዝማሬን አቀረቡ፡፡ ነገር ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ “ታላቅ ምልክት በሰማያት ታየ ፀሐይን ተጎናጽፋ ጨረቃን ተጫምታ በራሱዋም ላይ ዐሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች”(ራእ.12፡1)ሲል ስለ ጌታ ልደት ብቻ መናገሩ አልነበረም፡፡ ይህ ምልክት ከልደት እስከ ዕረገት በጌታችን ሥጋዌ የተፈጸሙትን የድኅነት ሥራዎችን ሁሉ የሚጠቀልል ነው፡፡እነዚህ የድኅነት ሥራዎች በምድር ይፈጸሙ እንጂ በሰማያዊው አምላክ የተፈጸሙ ናቸውና ፍጹም ሰማያዊያን ናቸው፡፡ ያም ማለት በቦታና በጊዜ የሚወሰኑ አይደሉም፤ ዘለዓለማውያንና ዘመን የማይቆጠርላቸው ናቸው፡፡ ምክንያቱም ዘመን በማይቆጠርለት አምላክ የተፈጸሙ ናቸውና፡፡ እነዚህን የድኅነት ሥራዎች ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው  ሰውነት የከወናቸው ናቸው፡፡

 ይህን ለመረዳት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታችን ሊቀ ካህንነት የጻፈልንን እንመልከት፡- “ክርስቶስ ግን ለምትመጣይቱ መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ የሰው ልጅ ወደ አልሠራት በዚህ ዓለም ወደ አልሆነችው ከፊተኛይቱ ወደምትበልጠውና ወደምትሻለው ድንኳን የዘለዓለም መድኀኒትን ገንዘብ አድርጎ በገዛ ደሙ አንድ ጊዜ ወደ መቅደስ ገባ እንጂ በላምና በፍየል ደም አይደለም”(ዕብ.9፡11-12)አለ፡፡ በዚህ ኃይለ ቃል ውስጥ ሐዋርያው ጌታችንን ሊቀ ካህናት እንዳለው እናስተውላለን፤ ስለዚህም መሥዋዕት አቅራቢው እርሱ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ “የሰው ልጅ ወደ አልሠራት በዚህች ዓለም ወደ አልሆነችው … ድንኳን” በመቀጠልም “መቅደስ” ያለው ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የነሣውን ሥጋና ነፍስ ሲሆን፤ ሰማይ ያለውም እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ነው፡፡ “በገዛ ደሙ” የሚለውም ኃይለ ቃል የሚያስረዳን ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡን ሲሆን ዘለዓለማዊ መድኀኒት ያለው ለእኛ መድኀኒት አድርጎ የሰጠውን ቅዱስ ሥጋውንና ክብር ደሙን ነው፡፡ ይህ አጠቃለን ስንመለከተው እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድ ራሱን መሥዋዕት፣ ራሱ መሥዋዕት አቅራቢ ሊቀ ካህናት ፣ራሱ መሥዋዕት ተቀባይ ሆኖ እኛን ከራሱ፣ ከእግዚአብሔር አብ፣ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፣ ጋር በገዛ ደሙ ፈሳሽነት መስታረቁን የሚያስረዳ ነው፡፡ ስለዚህም ወንጌላዊው ይህን ለማስረዳት“ታላቅ ምልክት በሰማይ ታየ” አለን፡፡
እንዲህ እንደሆነ ለማስረዳትም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “… እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርይ ምሳሌ ሆኖ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” አለን፡፡(ዕብ.1፡3) ይህ ኃይለ ቃል ጌታችን እንደ እግዚአብሔር በግነቱ መሥዋዕት ሆኖ ፤ እንደ ሊቀ ካህንነቱ በመስቀሉ መሠዊያ ላይ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ፤ እንደ እግዚአብሔርነቱ ደግሞ መሥዋዕቱን ተቀብሎ እኛን ከኃጢአታችን አንጽቶ ማረጉን የሚያስረዳ ኃይለ ቃል ነው፡፡  እነዚህን የድኅነት ሥራዎችን እግዚአብሔር ቃል ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሱዋ ነፍስ በመንሳት የፈጸማቸው፣ በእርሱ ብቻ የሚፈጸሙ ታላላቅ ምልክቶች ናቸው፡፡
 ቅዱስ ኤፍሬም በቅኔ ድርሰቱ ላይ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጁዋን ወዳጇን “ልጄ ሆይ አንተ የእኔን ውሱን የሆነ ሥጋና ነፍስ በመልበስ መልሰህ ለእኔ አለበስኸኝ” አለችው ይለናል፡፡ ስለዚህም ወንጌላዊው እርሱዋን “ፀሐይን ተጎናጽፋ” ሲለን ፀሐይ የተባለው ፀሐየ ጽድቅ የሆነውን ክርስቶስ መሆኑን እንረዳለን፡፡ እኛም ክርስቲያኖች በእርሱዋ ይሁንታ ምክንያት በጥምቀት ክርስቶስን ለብሰነዋል፡፡ ስለዚህም እርሱ የእርሱዋ ልጅ እንደሆነ እኛም በለበስነው በእርሱ ሰውነት በኩል በጸጋ የእርሱዋ ልጆች ሆነናል፡፡
“ጨረቃም ተጫምታ” በማለት በጨረቃ የተመሰልነው በእርሱዋ እናትነት ሥር ያለነው እኛ ክርስቲያኖች ነን፡፡ ይህን ለቤተ ክርስቲያንም ሰጥተን መተርጎምም እንችላለን፡፡ “ፀሐይን ተጎናጽፋ” የተባለችው ቅድስት ቤተክርስቲያን ናት ስንል ጌታችን እርሱዋን አካሉ በማድረጉ እርሱዋ በእርሱ መክበሩዋን ለማሳየት ነው፡፡ በጨረቃም የተመሰልነው ከጌታዋ ከሚመነጨው መለኮታዊ ብርሃን ብርሃንን ተቀብለን በመልካም ሥነ ምግባር አብርተን ለዚህ ለጨለማው ዓለም ብርሃናንን የምንሰጥ በራሳችን ግን ብርሃን አመንጪዎች ያልሆነው እኛ ነን፡፡ ይህን ለእናታችን ሰጥተን ከተረጎምነው ደግሞ ከእርሱዋ በነሣው ሰውነት በኩል ለእኛ የተገለጠውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል ለጨለማው ዓለም ብርሃንን የምንሰጥ መሆናችንን የሚስረዳ ነው፡፡ ስለዚህም “ፀሐይን ተጎናጽፋ” የሚለውን ኃይለ ቃል በነቢዩ ኢሳይያስ “ብርሃንሽ ወጥቶአልና የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶብሻልና ተነሺ አብሪ …”(ኢሳ.60፡1) ተብሎ አስቀድሞ ለተነገረላቸው ለእናታችን ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለቤተክርስቲያን እንደሆኖ እንረዳለን፡፡
 “በራሱዋ ላይ ዐሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆኑላት አንዲት ሴት ነበረች”  በማለት በዐሥራ ሁለቱ ከዋክብት ያላቸው ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እርሱን በእምነታቸው የመሰሉትንና በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የጸኑትን የፊልጵስዮስ ክርስቲያኖችን ሲያመሰግናቸው “ደስታዬና አክሊሌ የሆናችሁ ወንድሞቼ ሆይ”(ፊልጵ.4፡1)ብሎአቸው ነበር፡፡ በዚህም ቅዱስ ጳውሎስ እነርሱን አክሊሌ እንዳላቸው እናስተውላለን፡፡ እንዲሁ ሐዋርያትም የቅድስት እናታችን አክሊሎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ተግባራዊ የሆነ ክርስትናን፣ እግዚአብሔር አምላክን ደስ የሚያሰኙበትን የድንግልና ሕይወትን እንዲሁም ሰውነታቸውን የእርሱ ቤተመቅደስ የሚያደርጉበትን ጥበብ ከእርሱዋ የተማሩ ናቸውና፡፡ እንዲህም እንደሆነ እንረዳ ዘንድ “እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁ” አለን፡፡(2ቆሮ.11፡2)ንጽሕት ድንግል ያላት ቅድስት ድንግል ማርያምን ነው፡፡ ይህም የሚያስረዳን ሐዋርያት ለክርስትናዊ ሕይወታቸው እርሱዋን አብነት ማድረጋቸውን ነው፡፡
ሐዋርያው "እኛ ቅድስት ድንግል ማርያምን አብነት እንዳደረግን እናንተም ልታደርጉዋት ይገባችኋል" ሲል “እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ” በማለት አስተማረን፡፡ ከዚህ ኃይለ ቃል እኛም ልክ እንደ ሐዋርያት ቀዳማዊት ሔዋንን ሳይሆን ዳግማዊት ሔዋን የተባለችውን እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንድንመስል መጠራታችንን እናስተውላለን፡፡  
 እንዴት ነው ታዲያ እኛ ቅድስት ድንግል ማርያምን ልንመስላት የምንችለው? ለሚለው ጥያቄ ቅዱስ ኤፍሬም መልስ ይሰጠናል “ቅዱስ የሆነው እርሱ በሥጋ ከቅድስት ድንግል ማርያም መኅፀን አደረ፤ እንዲሁ በመንፈስ በነፍሱዋ አደረ፡፡… አሁንም እርሱ እርሱን ባወቁትና ነፍሳቸውን ንጽሕት ባደረጓት ሰውነት ውስጥ ማደሪያውን ያደርጋል፤ ስለዚህም ነፍሳችን ማደሪያው ትሆን ዘንድ ከኃጢአትና ከነውር ሁሉ ንጹሕት እናድረጋት” ይለናል፡፡ በእርግጥ ጌታችን “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም አንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን”(ዮሐ.14፡23) ብሎ እንዳስተማረን ፈቃዱን ፈጽመን ከተገኘን ሰውነታችንን የእርሱ ማደሪያ ማድረግ ይቻለናል፡፡ እንዲህ ሆነን ተገኘን ማለት ደግሞ እኛም እንደ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰውነታችንን ሰማይ አደረግነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እኛ መክብራችን በእርሱዋ ነውና እርሱዋ ለእርሱ ቅድስተ ቅዱሳኑ ስትሆን እኛ ግን መቅደሱ ነን፡፡
 ስለዚህም ቅድስት ሆይ ራስሽን ለጌታ ቅድስተ ቅዱሳን በማድረግ እኛን መቅደሱ እንድንሆን አብቅተሸናልና እንወድሻለን፡፡ ክብርት ሆይ ባንቺ ይሁንታ ከአንቺ ሥጋን በመንሳት እርሱን በጥምቀት አንድንለብሰው ምክንያት ሆነሽናልና እናከብርሻለን፡፡ ብፅዕት ሆይ ከአንቺ በመወለድ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ስላበቃሽን “ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” እንዳልሽው ብፅዕት ብለን  አናመሰግንሻለን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡      

2 comments:

  1. bejigu maraki yehon timihirit new yeabatochachin amilaki abizito segawin yisitihi enidemari yetafet yebatochichin timihirit silasitemarikeni kale hiyiewti yasemalini memihiri

    ReplyDelete