Sunday, January 22, 2012

“የከበረው መሥዋዕት”(በቅዱስ ይስሐቅ)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
14/05/2004

ልጄ ሆይ የአእምሮህን ምንጭ ንጹሕ አድርገው

ከቁጣና ከነቀፋ ቃልም አጽዳው

እንደ አዘቅት ጭቃ የሆነውን ቅናትን ከውስጥህ አስወግድ

አስተሳሰብህ ሁሉ ንጹሕ ይሁን፡፡

እግዚአብሔርን ለማየት በጸሎት ወደ እርሱ በቀረብክ ጊዜ

አንተን በሚጠባበቁህ በእግዚአብሔር የምሕረት እጆች ፊት ጸሎትህ ንጹሕና ቅዱስ ካልሆነ

ሥላሴ በአንተ አይታመንምና እንዲህ ሆነህ ከፊ አትቅረብ፡፡

ከበከተው ለእርሱ መሥዋዕት አታቅርብ

ለኃያሉ አምላክ ከአንተ ዘንድ የሚቀርበው መሥዋዕት

በቅናት የተቃኘ ጸሎት ከሆነ

የበከተ መሥዋዕት ማለት ይህ  ነው፡፡

ስለዚህ በአንተ ላይ በተቃጣው የቁጣ ቀስት ላይ ተጨማሪ ክብደትን አትጨምርበት

የተመረጥከው ወዳጄ ሆይ ! በሚያቃጥል ፍቅር የተቀመመ መሥዋዕትን አቅርብ

ለእርሱ እንደ መሥዋዕት አድርገህ የምታቀርበው ጸሎትህ ነው

እንዲህ ዓይነት መሥዋዕትን የሚያቀርቡት መንፈሳውያን ናቸው

ከአምላክ ዘንድ የሚቀርብ ይቅርታን የሚያሰጥ የጣፈጠ መሥዋዕት ይህ ነው፡፡

ስለዚህም በጥናህ ውስጥ ጠብ ካለ እርሱ ባዕድ ፍም ነው

እርሱንና እርሱን የመሰሉትን ፍሞች ከጥናህ ውስጥ አስወግዳቸው

 ልጄ ሆይ ባዕድ ፍምን በጥናህ ውስጥ በመጨመርህ ምን እንደሚመጣብህ አስበህ ፍራ

የአሮን ልጆች በድፍረት ያልታዘዙትን ፍም ከጥናቸው ውስጥ ጨምረው ነበርና በእግዚአብሔር ቁጣ ጠፉ (ሌዋ.፲፥፩-)

የመሥዋዕቱ ፍም ፍቅር ነው፤ በዚህም ፍም ላይ መሥዋዕት አድርገህ የምታቀርበውን ጸሎት አዘጋጅ

እንዲህ በማድረግህ ጸሎትህ የተወደደ መልካም መዓዛ ያለው ዕጣን ሆኖ ከእግዚአብሐር ዘንድ ይደርስልሃል

የፍቅር ፍም አመድ የለውም በመቀጣጠሉም ምንም ጭስ አይገኝበትም

በውስጡ ዘለዓለማዊና ጣፋጭ መዓዛ ያለው መሥዋዕትን ይዞአል

ደስ ከሚያሰኙ መሥዋዕቶችም በላይ እጅግ የላቀና የከበረ መሥዋዕት ይህ ነው፤

ክርስቲያን ሆይ ይህን ልብ በል!!(ከአብርሃም ሶርያዊ)


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
13/05/2004
ወገኔ ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ፣ የእግዚአብሔር ወዳጆች ለተባሉት ወንድም/እኅት/ ፣ ከሐዋርያትና ከሰማዓታት ጋር ከበዛው ጸጋቸው ተካፋይ ፣ ከእርሱም ምስክሮች ጋር አንድ ማዕድን የምትካፈል ፣ የቅዱሳን ርስት ወራሽና ቅን በሆነው ፍርዱ ደስ ይልህ ዘንድ ከነቢያት የፍርድ ወንበር ላይ የተቀመጥክ ፣ ከቅዱሳን መላእክት ጋር በምስጋና የምትሳተፍ ፣ ከሱራፌልም ጋር የምትነጋገር ፣ ከኪሩበል ጋር በሰማያዊ ዙፋን ላይ የተቀመጥክ ፣ ከክርስቶስ የጸጋ ስጦታ ተካፋይ የሆንክ ፣ የብቸኛ ልጁ ሰርግ ታዳሚ ትሆን ዘንድ የተጠራህ ፣ የሰማያውያን ሠራዊተ መላእክት ወዳጅ ፣ የሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ዜግነት ያለህ ነህ ፡፡ አእምሮህ ውስጥ እነዚህ በክርስቶስ ለአንተ የተሰጡት የእግዚአብሔር ቸርነቶች ከተቀመጡ የጨለማው ዓለም ገዢ አገልጋዮች የሆኑ አንተን ሊያሰነካክሉህ አይችሉም ፡፡ በንስሐ ጽና ፡፡ ሕሊናን ከሚያቆሽሹ ከንቱ አስተሳሰቦች ራስህን ንጹሕ አድርግ ፡፡ ከእነዚህ ፈጽመህ ራቅ ከንቱ በሆኑ አስተሳሰቦችም አትሸበር፡፡”