Wednesday, December 12, 2012

ክብርት ስለሆነችው ሥጋችንና በእርሱዋ የእግዚአብሔር ፈቃድ



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
04/04/2005 ዓ.ም
ሥጋ ክብርት ናት፡፡ ገናም ከአፈጣጠሩዋ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረች ናት፡፡(ዘፍ.9፡6) የማይታየው የእግዚአብሔር መልክና ባሕርይ የሚታየው በሚታየው በሥጋ ተፈጥሮአችን በኩል ነው፡፡ የእግዚአብሔርን መልክና ክብር በክርስቶስ አይተነዋል፡፡ እኛንም ማዳኑ በሥጋው ሰውነቱ ነው፡፡ ተወለደ፣ በየጥቂቱ አደገ፣ ደከመ፣ አንቀላፋ፣ ታመመ፣ ተጨነቀ፣ ተሰቃየ፣ ሞተ መባሉ በሥጋው ነው፡፡
ሰውነታችን ከምድር አፈር መፈጠሯም በራሱ ሥጋን ቢያልቃት እንጂ የሚያሳንሳት አይደለም፡፡ ምድር በመኅፀኑዋ ሕይወትን፣ ኃይልን፣ ውበትን፣ መድኀኒትን፣ ለፍጥረት ሁሉ ምግብ የሆኑ በዓይነትና በብዛት እንዲሁም በይዘት እጅግ ብዙ ንጥረ ነገሮችን ሰውራና አቅፋ የያዘች ናት፡፡ እነዚህ ንጥረ ነገሮች ከሰማይ በሚወርደው ዝናብ ምክንያት ተብላልተውና ተስማምተው በእግዚአብሔር ጥበብ ለፍጥረት ሁሉ ምግብን፣ ፈውስን፣ ውበትና ኃይልን ሲሰጡ ይኖራሉ፡፡ ይህን አስመለክቶ እግዚአብሔር “በዚያ ቀን እመልሳለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ለሰማይ እመልሳለሁ ሰማይም ለምድር ይመልሳል ምድርም ለእህልና ለወይን ጠጅ ለዘይትም ትመልሳለች፡፡”(ሆሴዕ.2፡23)ይለናል፡፡