በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
11/04/2010
ሕግ የእግዚአብሔር ባሕርይንና ፈቃድ የምንለይበት መሣሪያ ነው፡፡ ነገር ግን ሰው በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል የተፈጠረ ፍጥረት ስለሆነ በባሕርይው የእግዚአብሔርን ባሕርይና ፈቃድ ያውቃል፡፡ ሰው ለባሕርይው አልታዘዝ ሲል የገዛ ተፈጥሮውን ወደ ማጥፋት ይመጣል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰው በልቡናው ወይም በተፈጥሮ ውስጥ ያኖረውን ሕግ በማጥፋቱ ፈጽሞ ጠፍቶ እንዳይቀር በጽሑፍ ሕግን ሠራለት፡፡ ይህ በጽሑፍ የተዘጋጀው ሕግ የሚያስፈልገው ሕግን ላፈረሱ ኃጥአን እንጂ ለጻድቃን አልነበረም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር “ሰው እንደሚገባ ቢሠራበት ሕግ መልካም እንደሆነ እናውቃለን ይኸውም ለበደለኞች ቅድስና ለሌላቸውና ለርኩሳን ….ሁሉ እንደ ተሠራ እንጂ ለጻድቅ እንዳልተሠራ ሲያውቅ ነው ፡፡”(1ጢሞ.1፡8-11) ይላል፡፡ ስለዚህ የጽሑፉ ሕግ የተሰጠን ለእርሱም የአፈጻጸም ሥርዓታት የተሠሩት እኛ ከልቡና ሕግ በመውጣታች ነው፡፡ ጻድቃን ግን ሕግን ሳይጠብቁ ሕግን ይፈጽማሉ፡፡ ይህም እግዚአብሔርንና ባልጀሮቻቸውን ከማፍቀራቸው የተነሣ ነው፡፡ እነርሱ የሚተጉት በትሩፋት ሥራዎች ላይ ነው ፡፡ የትሩፋት ሥራዎች የሚባሉት በምጽዋት፣ ነፍስን በማዳን፣ በንጽሕና በመመላለስ፣ እና በመሳሰሉ ተግባራት ላይ ነው፡፡ ይህንን ከፍቅር ስለሆነ የሚተገብሩት ሕግን እየፈጸሙ እንደሆነ አያስተውሉትም ፡፡ ስለዚህም ጌታችን ቅዱሳንን በምጽአት ስራብ አብልታችሁኛል ስታሰር ጠይቃችሁኛል ብሎ ሲያመሰግናቸው ጌታ ሆይ መች ተርበህ አይተንህ አበላንህ መች ተጠምተህ አይተንህ አጠጣንህይሉታል ፡፡(ማቴ.25፡35-40) ስለዚህ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ግቡ እግዚአብሔር አምላኩን መምሰል ነው ለዚህም ይተጋል እንደ ትጥቅም የሚታጠቀው ፍቅረ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን ነው፡፡ ሰው ለፍቅር ሲገዛ ሕግጋትን አሟልቶ መፈጸም ይችለዋል፡፡ ሕግ ወደ ፍቅር የሚያደርስ መሠላል እንጂ በራሱ ፍጻሜ አይደለም ፍጻሜው ክብር ይግባውና በእርሱ አማልክት መሰኘት ነው፡፡