ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
07/01/2005
እናንተዬ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስፈልጋት እንደው አሻጉሊት የሚሆን ራስ ነው እንዴ? ይህ እኔን እጅግ ያንገሸገሸኝ እኔን
ብቻ ሳይሆን መላው ምእመናንን ያስመረረ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን እኛ የምንፈልገው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብትና የሰው ኃይል በአግባቡ
ተጠቅሞ በመንፈሳዊውም በኢኮኖሚያዊም መስክ ክርስቲያኑን ማኅበረሰብ የሚያበቃ በሳል ሊቀጳጳስ ነው ነገር ግን አሁንም እንደቀድሞው
አሻጉሊት የሆነ ራስ ራስ ሊሆን ከመጣ ራስነቱ ለራሱ ይሁን እኔ ግን ቅርብኝ ብያለሁ፡፡ በቃኝ
ቅርብኝ ቅርብኝ
ራስ እኔነቴን ካዋረደ፤
እፍረትን በእኔ ላይ ካንጓደደ፤
እኔስ እንዴት ላክብረው ራሴን?
ቁልቁል ከጣለው ማንነቴን?
እረ ወዲያ በቃኝ ራስነቱ
ይቅርብኝ፤
ጡረተኛን ጣሪ አካል
ካደረገኝ፤
ካልጠቀመኝ ራስነቱ፤
ካልረባን አክሊልነቱ፤
እረ ወዲያ ይቅርብኝ፤
ራሱ ገምቶ አካሌን
አያግማው፤
ራሱ ያመጣውን ራሱ ይወጣው፤
በሕሊናዬም አይታሰብ ስም አጠራሩም አይታወስ፤
ሰላሜን አይንሳ ብስጭቴን አይቀስቅስ፡፡
ግና እግዚአብሔር በእርሱ ከነገሠ ፤
ነፍሱን ለጌታው ፈቃድ ካፈሰሰ፤
ይምጣ ይግባ ራስም ይሁነኝ፤
በርቶ ያድምቀኝ ሞቆ ያሙቀኝ፤
ሕያው ሆኖ ያኑረኝ ብርሃንን ያልብሰኝ፤
ያለበለዚያ ወዲያ ወዲያ ክላልኝ አትምጣብኝ፡፡
ጫንቃዬ ሰልችቶአል ጡረተኛን ማዘል፤
እሹሩሩ ማለት ጡጦ እየሰጡ ማባበል፡፡