በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ቀን ሰኞ 30/05/2003
አዲስ አበባ
እግዚአብሔር በባሕርይው ፍቅር ነው፡፡ እርሱ እጅግ ጥልቅ ከሆነው ለእኛ ለሰዎች ከመረዳት ባለፈ ፤ በእርሱ ብቻ በሚታወቅ ፍቅር ውስጥ ይኖራል፡፡ ሰውን በእርሱ አርዓያና አምሳል ፈጠረው ስንልም በባሕርይው ፍቅር የሚስማማው አድርጎ ፈጠረው ስንል ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ሰዎችን እጅግ ይወዳል፡፡ ሰውን በማንኛውም ማለትም በትልቅም ይሁን በትንሽ ባለማወቅም ይሁን በድፍረት በስውርም ይሁን በግልጽ በተንኮልም ይሁን በተግዳሮት የምናሳዝነው ከሆነ የምናሳዝነው ሰውየውን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ጭምር ነው፡፡ በእኛ ያዘነው ሰው ልቡ በሃዘን ሲሰበር፤ እግዚአብሔርም እጅግ ያዝናል፡፡ በሃዘን ውስጥ ያለውን ሰው ከልቡ ደስ እንዲሰኝ ስናደርገው እግዚአብሔርም ደስ ይለዋል፡፡ በቅንነት ወደ ሰዎች ሁሉ ስንቀርብ እርሱም ከእኛ ጋር በቅንነት ይቀርባል፡፡ ሰዎችን ሁሉ እኩል ስናይለት ልቡ በደስታ ትፈካለች፡፡ በተንኮል ስንቀርብ ግን ግርማው ብቻ እንደሚያርድ አንበሳ በቁጣው ያርበደብደናል፡፡ በክፋታችን ከጸናን ደግሞ ያደቀናል ከእርሱ እጅ የሚታደገን ማንም አይኖርም ፡፡ ክፋታችንን አውቀን ከልባችን መጸጸታችንን ሲመለከት ደግሞ ልጁዋን እንደምታፈቅር እንስፍስፍ እናት ኃጢአታችንን ሁሉ ረስቶ በጸጋዎቹ እየሳመን ያጽናናል፤ ከእቅፉ ውስጥም በማኖር በፍቅሩ ያሞቀናል፡፡ የእርሱ ሃዘን ሰዎች ፍቅር ያጡ ጊዜ ነው፡፡
እግዚአብሔር እርሱን የሚጠሉትንም የሚወዱትንም ይወዳል፡፡ ይህንንም ፍቅሩን በክርስቶስ አይተናል፡፡እርሱ በቃሉ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ” አለን፡፡ ስለፍቅር ስትሉ ወደ እናንተ ሊበደር የመጣውን ሰው አትከልክሉት፣ የሚያሳደዱአችሁን መርቁ፣ኮትህን ለሚለምን መጎናጸፊያህንም ተተውለት፤ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ፣ አንድ እርምጃ እንድትሄድ ለጠየቀህ ሁለት እርምጃ ሂድለት፤ ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ እንዲመልስም አትጠይቀው፣ የበደለህን ይቅር በል በሎ አስተማረን፡፡ በተግባርም ለለመኑት ሁሉ ሰጠ፡፡ ግብር እንዲገብርም በተንኮል ለጠየቁትን የእርሱን ብቻ ሳይሆን የጴጥሮስንም ግብር ከፈለ፡፡ እኛን ጠላቶቹን ወደደ፣ ከእርሱ ሊበደሩ ለመጡት ሁሉ አልከለከለም፤ ስለሚያሳደዱት በመስቀሉ ላይ “የሚያደርጉትን አያውቁምና አባት ሆይ ይቅር በላቸው” ብሎ ጸለየ፡፡ ይህ ሁሉ ተግባሩ እኛ በቃልም በተግባርም፣ ፍቅርን አንዳናጠፋ አርዓያ ሊሆነን ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም ስለፍቅር ስትሉ ለበላይ ባለሥልጣኖቻችሁ ታዘዙ፣ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ ፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን ስጡ፡፡ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ፡፡ በወንድምህ ላይ አትፍረድ፣ደካማውን በድካሙ ላይ አትፍረዱ ይልቁኑ ድካሙን ተሸከምለት፣ከአዘነው ጋር እዘኑ ደስ ካለው ጋር ደስ ይበላችሁ፡፡ በእምነታቸው አብነት የሆኑዋችሁን ወኖቻችሁን ምሰሉዋቸው፡፡ በእድሜ የሚበልጡዋችሁን አባቶችን እንደ አባት እናቶችንም እንደ እናት ፣እኩዮቻችሁንም እንደ ወንድምና እንደ እኅት ተመልከቱአቸው፡፡ ቤተሰቦቻችሁን ውደዱ፡፡ የገዛ ቤተሰቡን የማይወድ ከማያምንም ሰው የከፋ ሰው ነው በማለት መለያየትን ከሚያመጡ ነገሮች ሁሉ እንድንርቅ አዘዘን፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስም ስለፍቅር ስንል ለክፉ ጌቶቻችንም እንድንታዘዝ፣ በኃይማኖትም ለሚከራከሩን በየዋህነት እንድንመልስላቸው፣ ስለፍቅር ስንል ጠጉራችንን ከመሾረብ ውድና ጌጠኛ ልብሶች ከመልበስ፣በአልማዝና በወርቅ አንዲሁም በብር ከመጌጥ ይልቅ በሰውነታችን ቤተመቅደስ ያደረውን በስውር ያለውን ክርስቶስን እንድንለብሰውና በእርሱ ተጊጠን እንድንገኝ መከረን፡፡ መድኃኒታችን፣ ፈጣሪያችን፣ ሕይወታችን፣ ትምክታችን፣ መሸሸጊያችን፣ ናፍቆታችን፣ ብርሃናችን፣ መንገዳችን፣ መድረሻችን፣ ገነታችን፣ መንግሥተ ሰማያታችን፣ አፍቃሪያችን፣ አባታችን የሆነን እርሱ ወንድሞቹና እኅቶቹ ያደረገን እውነት፣ ፍቅር የተባለውን ጌታችንን የሚያርቁ ማናቸውንም ነገሮችን በአንደታችን እንዳናወጣቸው በተግባርም እንዳንፈጽማቸው አጥብቆ አዘዘን፡፡ ምክንያቱም ፍቅርን ከማፍረስ የበለጠ እርሱን የሚያሳዝን ነገር የለምና፡፡ እርሱ በሰዎች ላይ ያለው ዓለማ ፍቅር ነው፡፡ ስለዚህም ቸልተኝነት፣ መልካምን ለመሥራት እየቻሉ አለመሥራት፣ ፊት መንሳት፣ እርዳታን ላለማድረግ ሕግን ምክንያት ማድረግ፣ የራስ ጥቅምን ማስቀደም እርሱን ያሳዙኑታል፡፡ አንድ ሰው በልቡናችን የሚመላለሰውን ክፉ አሳብ ስለማያውቅ በእኛ ላይ ላይከፋ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ግን በልባችን የሚታሰቡ ክፉ አሳቦችን ሁሉ ያውቃልና ከሰው ቀድሞ በእኛ ይከፋል፡፡
በመለየያት፣በጀብደኝነት፣በኩራት፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በቀለም. እያፎካከረ አላዋቂነታቸውን ተጠቅሞ ከሚገዛቸው ከሰይጣን ባርነት ነፃ አውጥቶ በፍቅር ልክ በሰማያት እንዳሉ ቅዱሳን መላእክት ብዙ ሲሆኑ አንድ፤ አንድ ሲሆኑ ብዙ ያደርጋቸው ዘንድ የመጣው መድኃኒታችን ክርስቶስ ዓለማው ፍቅር ነው፡፡ ክህደት ወይም ምንፍቅና እጅግ የከፋ ኃጢአት የሆነበትም ምክንያት ፍቅርን አጥፍቶ መለያየትን ስለሚያነግሥ ነው፡፡ መልካም የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት አለመፍቀድ፣ ምን አገባኝ ማለት፣አይመለከተኝም ማለት፣ አላውቅም ማለት፣ ሲቻል አልችልም ማለት፣ ሰዎችን የሚያፈቅረውን እግዚአብሔርን ያሳዝኑታል፡፡አምላኬ ሆይ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ይህን ማስተዋል ትሰጠኝ ዘንድ እለምንሃለሁ፡፡ ሁሌም በምድራዊ ሕይወቴ ፍቅርን የማስቀድም ከሆነ ጌታ ሆይ አንተን ደስ ስለማሰኝህ ነፍሴም መንፈሴም ሥጋዬም በደስታህና በፍቅርህ ይሰክራሉ፤ አቤቱ ማስተዋልን ስጠኝ፡፡ ማስተዋሌ ሌሎችን በተንኮል የማሰናክልበት ሳይሆን የምትወዳቸውን የሰውን ዘር ሁሉ ደስ አሰኝበት ዘንድ የሚያገለግለኝ የፍቅርህ ባሪያ ይሁንልኝ፡፡ አሜን
No comments:
Post a Comment