Sunday, January 15, 2012

የተባረከው ሩካቤ (ለሙሽሮች)



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
19/02/2003 ዓ.ም
አዲስ አበባ


ባልና ሚስትን ሰማያዊ ወደ ሆነው የደስታ ሥፍራ እንዲነጠቁ የሚያደርጋቸው፤ ፍቅር ከሞላበት ኩልል ካለው ከብርሃናዊ ምንጭ ጠጥተው የሚረኩበት፤ የደስታን እንባ በማንባት በፍቅር ግለት ልክ ከእናቱ ማኅፀን ግሩም በሆነ ጥበብ በእግዚአብሔር እጅ እንደሚፈጠር እቦቀቅላ ሕፃን አንድ አካል ለመሆን በእግዚአብሔር የሚሠሩበት ማኅፀን፡፡
የጌታን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በየእለቱ አንድንቀበል በዚህም ወደሰማያዊ ምንድግናና ከክርስቶስ ጋር ፍጹም ወደሆነ ተዋሕዶ አንደምናድግ፤ እንዲሁ በዚህ የተባረከ ሩካቤ እግዚአብሔር ፍጹም ወደሆነ የአካል፣ የመንፈስ፣የስሜት ፣የፈቃድ አንድነት እንድንመጣ ለመላእክት ያይደለ ለእኛ ...ለሰው ልጆች ብቻ በእጁ ከምድር አፈር እንዳበጀው አዳም ሆነን ዳግም እንድንፈጠር የተሰጠ ግሩም ስጦታ፡፡

ቀስ በቀስም በአንድ አካል ወደምንገለጥበት ከፍታ የምንሸጋገርበት ልዩ የእግዚአብሔር በረከት፡፡ ከአንድ አዳም ከአጥንቱ አጥንት ከሥጋው ሥጋ ከነፍሱ ነፍስ በመንሳት ሔዋን ልጁ እንደ ተወለደች፣ በአዳማዊ ጥምረት አንድ አካል የሆኑት እነዚህ ጥንዶች የተዋሕዶአቸውን ፍሬ በዐይናቸው ይመለከቱ ዘንድ ከአብራካቸው ድንቅ የሆነን ሥጦታን ከእግዚአብሔር የሚቀበሉበት የዕረፍት ሥፍራ፡፡
ኦ አምላኬ የጥንት ፈቃድህን ታሳውቀን ዘንድ በተግባር ከአዳም ሔዋንን ያስገኘህ (ዘፍ.2፡2) በቃልህም “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡”(ዘፍ.3፡23) እንዲሁም..“እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው::”(ማቴ.19፡6)በማለት ያስተማርከን ይህ ትምህርት እንዴት ግሩምና ድንቅ የሆነ ምሥጢርን በውስጡ ይዟል፡፡
ጌታ ሆይ ለሰው ልጆች እንጂ ለመላእክት ባልሠራኸው በዚህ ድንቅ ስጦታህ ጥንዶች ሁሌ ያመሰግኑሃል፡፡ ክብር ለአንተ ለወደድከን በተባረከውም በዚህ ሩካቤ ላበዛኸን በእርሱም ጥልቅና ጥብቅ የሆነውን ፍቅር በደም በአጥንት እንዲሁም በሥጋችን ላሰረጽከው ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡ “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል፡፡”(ዕብ.12፡4)

1 comment:

  1. awo gabicha kidusi new kale hiyiweti yasemalin wenidimachin

    ReplyDelete