Sunday, January 15, 2012

የአምላክ እናትነት




ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ቀን 4/06/2003 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ጌታ ሆይ የእጅህ ሥራ ስለሆንኩ እጅግ ግሩምና ድንቅ ነኝ፡፡ ስለኃጢአቴ ራሴን ብወቅስም አንተ ግሩምና ድንቅ አድርገህ የፈጠርከውን ሰውነቴን በኃጢአቴ ምክንያት የተዋረደ ነው አልለውም፡፡ ይህ ሰውነት በአንተ ንጹሐን እጆች የተበጁ ናቸውና፡፡

እናቴ ሆይ ንገሪኝ አንቺ ትሆኝ ከሆድሽ ሳለሁ ሰው እንድሆን ዐይንና ጆሮ አፍንጫንና ግንባርን የሠራሽልኝ፣ ወይስ አንቺ ትሆኚ ሥጋዬን ከአጥንቴ ጋር አዛምደሽ ያበጃጀሻቸው? ወይስ በሥጋዬ ውስጥ ደምሥሮቼንና ጅማቶቼን አንዲሁም ልብና ኩላሊቴን ሌሎችንም ውስብስብ የሆኑ የሰውነት ሥርዐቶችን የሠራሻቸው? አንቺ ከሆንሽ በምን እውቀትሽ? እንዲህ ከሆነ ከእናቴስ በላይ አዋቂ ማን አለ? ከእናቴስ በላይ ሁሉን ቻይ ማን አለ? ነገር ግን እናቴ ዐይኖቹዋን በፍቅር ወደ አምላኩዋ አቅንታ “አንተን ከእኔ እኔንም ከእናቴ ማኅፀን ያበጀኝ እርሱ እግዚአብሔር ነው” ብላ አመላከተችኝ፡፡ ከልቡዋም ሆና እርሱዋን ሠርቶ በእርሷ ልጆቹዋን የፈጠራቸውን አምላኩዋን ዐይኖቹዋ የፍቅርን እንባ አንዳጋቱ ሲጋ እየተናነቃት ወደ እርሱ አንጋጠጠች፤ ተንበርክካም ስለቸር ስጦታው አመሰገነችው፡፡ በግንባሩዋም ተደፍታ ሁሉን እንዲህ ላከናወነው ለእርሱ ሰገደችለት፡፡ ከሰጊዱዋም ቀና ስትል ጉንጮቹዋ በእንባ ረጥበው ነበር፡፡ ዐይኖቿንም አቅንታ ክርስቶስ ከሥጋዋ ከፍሎ ወደ ፈጠራቸው ልጆቹዋ ተመለከተች፡፡ ነገር ግን እንባዋ ከጉንጮቹዋ መጉረፉን አላቋረጠም ፡፡ ምክንያቱም ጌታ ሆይ የአንተ እጅ ሥራ ናቸውና፡፡

ከእርሱ ከሠሪው እግዚአብሔር በቀር ስለሥጋችንና ነፍሳችን ፍጹም ተዋሕዶና ክብር መርምሮ የሚረዳ ሰው ማን ነው? ቅዱሳን መላእክት ወይም ቅዱሳን ጻድቃን የሰውን ተፈጥሮና ክብር ዘርዝረው ሊገልጹት አልተቻላቸውም፡፡ ጌታ ሆይ አንተ እንደሳር ፈጥነው ይጠፋሉ ብለህ የተናገርክላቸውን የምድር ፍጥረታትን እንኳ ከአንተ በቀር ስለአፈጣጠራቸው ጠንቅቆ የሚናገር የለም ፤ አንተ ብቻ ሠሪያቸው የሆንክ ታውቃቸዋለህ እንጂ ከፍጥረት ወገን ማንም ተመራምሮ ሊደርስባቸው አይቻለውም፡፡ እወቁት ብለህ ብትሰጣቸው እንኳ ለዚህ እውቀት ፍጻሜ የለውምና እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ ስለገለጥክላቸው እውቀት ቢመራመሩ ጠንቅቀው ሊደረሱበት አይቻላቸውም፡፡ መላእክት ስለራሳቸው ሥነ ተፍጥሮአዊ አወቃቀር መናገር አይቻላቸውም፡፡ ነገር ግን ጌታ ሆይ ይህንን እውቀት እጅግ በሚልቅ እውቀት ተካኸው፡፡ ሰው ስለራሱ ቢመራመር አፈጣጠሩን ቢያውቅ በምድር ላይ ስላሉን ሥነፍጥረታትም ቢረዳ ከእነርሱ ያገኘው እውቀቱ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ቢመራው እንጂ አይቤዠውም፡፡ ሥነፍጥረታትን ሁሉ ብናቅ ለእኛ ከሚሰጡን አገልግሎት የተነሣ በሥጋችን ተጠቃሚዎች ብንሆን የሚያድነንን እውቀት ከእነርሱ አናገኝባቸውም፡፡ ዘለዓለማዊ ሕይወትንም አያሰጡንም፡፡ ምክንያቱም ጌታ ሆይ አንተ በሚበልጠው ተክተኸዋልና፡፡ ስለሆነም በእነዚህ ላይ አስቀድመን እንዳንተጋ አዘዘከን፡፡ አስቀድማችሁ ጽድቁንና መንግሥቱን እሹ ሌላው እንደ ድርጎ ይጨመርላችኋል ብለህ አስተማርከን፡፡ ግሩምና ድንቅ የሆነው ሥራህን እጅግ ግሩምና ድንቅ በሆነው ስጦታህ ለወጥከው፡፡ እርሱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ጌታችን ሆይ ስለእኛ መተላለፍ ፍርዳችንን ትቀበል ዘንድ ወደዚህ ዓለም መጣህ፡፡ እናትነትንም እጅግ ታከብረው ዘንድ ከድንግል ማርያም ማደሪያህን አደረግህ፡፡ ካደርክበትም ማኅፀን ሆነህ ለራስህ መገለጫ ይሆን ዘንድ ከሥጋዋ ሥጋ ከፍለህ ከነፍሱዋም ነፍስን ነስተህ ሰው ሆንህ፡፡ እንደ ሰውም የመወለጃ ወራት ተቆጥሮልህ ተወለድክ፡፡ ጎስቁሎ የነበረውን ሕይወታችንን ባንተ ልደት አጣፈጥከው፡፡ በዚህ ብቻ ግን አላበቃህም፡፡ ከአንተ ጋር አንድ ሥጋና አጥንት የምንሆንበትን የጥምቀት ሥርዐትን ሠራህልን፡፡ በጥምቀት በልደትህና በሞትህም ከአንተ ጋር ተባበርን፡፡ ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እናንተ ከአጥንቱ አጥንት ከሥጋው ሥጋ የሆናችሁ የክርስቶስ የአካሉ ክፍሎች ናችሁ” ብሎ መሰከረ፡፡(፩ቆሮ.፲፪፥፳፯) አሁን በአንተ አካል ተጠቅለለናል፡፡ አንተ እንደ ሰው ተወልደህ እኛን ልዩ በሆነ ልደት በጎንህ በፈሰሰው ቅዱስ ውኃና ደምም ዳግም ወለድንኸን፡፡ ስለዚህም ሐዋርያው “እኛ ፍጥረቱ ነንና አንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን፡፡”ብሎ መሰከረ(ኤፌ.፪፥፱-፲)፡፡ ስብሐት ለልደትህ ስብሐት ልስቅለትህ ይሁን አሜን!!


2 comments:

  1. ጌታችን ሆይ ስለእኛ መተላለፍ ፍርዳችንን ትቀበል ዘንድ ወደዚህ ዓለም መጣህ፡፡ እናትነትንም እጅግ ታከብረው ዘንድ ከድንግል ማርያም ማደሪያህን አደረግህ፡፡ ካደርክበትም ማኅፀን ሆነህ ለራስህ መገለጫ ይሆን ዘንድ ከሥጋዋ ሥጋ ከፍለህ ከነፍሱዋም ነፍስን ነስተህ ሰው ሆንህ፡፡ እንደ ሰውም የመወለጃ ወራት ተቆጥሮልህ ተወለድክ፡፡ ጎስቁሎ የነበረውን ሕይወታችንን ባንተ ልደት አጣፈጥከው፡፡ በዚህ ብቻ ግን አላበቃህም፡፡ ከአንተ ጋር አንድ ሥጋና አጥንት የምንሆንበትን የጥምቀት ሥርዐትን ሠራህልን፡፡ በጥምቀት በልደትህና በሞትህም ከአንተ ጋር ተባበርን፡፡ ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እናንተ ከአጥንቱ አጥንት ከሥጋው ሥጋ የሆናችሁ የክርስቶስ የአካሉ ክፍሎች ናችሁ” ብሎ መሰከረ፡፡(፩ቆሮ.፲፪፥፳፯) አሁን በአንተ አካል ተጠቅለለናል፡፡ አንተ እንደ ሰው ተወልደህ እኛን ልዩ በሆነ ልደት በጎንህ በፈሰሰው ቅዱስ ውኃና ደምም ዳግም ወለድንኸን፡፡ ስለዚህም ሐዋርያው “እኛ ፍጥረቱ ነንና አንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን፡፡”ብሎ መሰከረ(ኤፌ.፪፥፱-፲)፡፡ ስብሐት ለልደትህ ስብሐት ልስቅለትህ ይሁን አሜን!!GIRUMI AGELALESI SEGAWIN YABIZALI YAGELIGILOT ZEMENIHIN YARIZIMEWI

    ReplyDelete
    Replies
    1. “እኛ ፍጥረቱ ነንና አንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን፡፡”ብሎ መሰከረ(ኤፌ.፪፥፱-፲

      Delete