ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
05/04/2004
አዲስ አበባ
እጅግ ጠንቅቄ የማውቀው አንድ ሰው ነበር ፡፡ በእጁ ምንም ስባሪ ሳንቲም የለም ፤ ጸጉሩም አድጓል ፡፡ በእጁ ምንም ባለመኖሩ ምክንያት ጸጉሩ ቢያድግም መከርከም አልቻለም ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሌላም የገንዘብ እዳ አለበትና ጭንቅ ይዞታል ፡፡ ወዲያው አንድ ነገር ትዝ አለኝ፤ ለራሴ“በእውኑ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጉሩን ያሳደገው ከድህነት የተነሣ ይሆንን? አልኩኝ ፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው “ለወንድ ጠጉርን ማስረዘም ነውር ነውና”(፩ቆሮ.፲፩፥፲፬፣፲፭) ድህነት ደግሞ ለዚህም ያጋልጣል ፡፡
ጌታችንም ያደገው በምድራዊው ሀብት ደሃ ከምትባለው በሰማያዊው ብልጥግና ግን እጅግ ባለጠጋ ከሆነችው ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥር ሆኖ ነው ፡፡ ሐዋርያት “እኛ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን”(፪ቆሮ.፱፥፲፪) ካሉ ቅድስት ድንግል ማርያም እንዴት ከእግዚአብሔር ዘንድ ባላት ሞገስ የተነሣ ከጸጋ ተራቁተው ያሉትን ባለጠጎች አታደርግ ? እርሱዋ የክርስቲያኖች ሁሉ ተማሳሌት የሆነች ፣ ራሱዋን በቅድስና ሕይወት በማመላለስ እግዚአብሔር ለሌላ የማይፈጽመውን ወደ እርሱዋ በመምጣት በሥጋ ከእርሱዋ በመወለድ እናቱ ትሆን ዘንድ የመረጣት ፣ እውነተኛ እናቱ ናት ፡፡ ቢሆንም በምድራዊ ብልጥግና በእርግጥም ደሃ ነበረች ፡፡ “እፎ ቤተ ነዳይ ኀደረ ከመ ምስኪን እምሰማያት ወረደ ላዕሌሃ ፈቲሖ ሥነዚአሃ ወተወልደ እምኔሃ” እንዲል፡፡
እናም ለራሴ የጠየቅሁትን ጥያቄ ራሴ መለስኩት እንዲህም አልኩኝ ፡- የለም የለም እርሱ ናዝራዊያን እንደሚባሉት ገና ከእናታቸው ማኅፀን ለእግዚአብሔር የተሰጡትን ስለሚመስል ናዝራዌ ተባለ ብዬ መለስኩ ፡፡ ቢሆንም ናዝራዊያን ጠጉራቸውን ካለመቆረጣቸው በተጨማሪ የወይን ጠጅ እንዲጠጡ አልተፈቀደላቸውም ነበር ፡፡ ጌታችን ግን እንዲህ አላደረገም ስለዚህ “የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ እነርሱም፡- እነሆ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ አሉት”(ማቴ.፲፮፥፲፱) ተብሎ ተጻፈለት ፡፡ ማቴዎስም ክርስቶስ ናዝራዊ የተባለው ናዝሬት በማደጉ ነው ይለናል “በነቢያት ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ አደገ”(ማቴ.፪፥፳፫)እንዲል፡፡ አንድ ነገር ግን አለ እርሱም ክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው፤ እርሱ በተናቀችው አህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ ይህም በእርሱ ዘንድ ከሥነፍጥረት የተናቀ እንደሌለ ያስረዳናል፡፡ ስለዚህም ከደሃ ቤተሰብ ተወለደ፡፡ ሌላውን ትርጉም መሠረታዊ ከሆነው ዋና ቁም ነገር ጋር ላለመደባለቅ ለጊዜው ትቼዋለሁ ፡፡
እናም ለራሴ የጠየቅሁትን ጥያቄ ራሴ መለስኩት እንዲህም አልኩኝ ፡- የለም የለም እርሱ ናዝራዊያን እንደሚባሉት ገና ከእናታቸው ማኅፀን ለእግዚአብሔር የተሰጡትን ስለሚመስል ናዝራዌ ተባለ ብዬ መለስኩ ፡፡ ቢሆንም ናዝራዊያን ጠጉራቸውን ካለመቆረጣቸው በተጨማሪ የወይን ጠጅ እንዲጠጡ አልተፈቀደላቸውም ነበር ፡፡ ጌታችን ግን እንዲህ አላደረገም ስለዚህ “የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ እነርሱም፡- እነሆ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ አሉት”(ማቴ.፲፮፥፲፱) ተብሎ ተጻፈለት ፡፡ ማቴዎስም ክርስቶስ ናዝራዊ የተባለው ናዝሬት በማደጉ ነው ይለናል “በነቢያት ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ አደገ”(ማቴ.፪፥፳፫)እንዲል፡፡ አንድ ነገር ግን አለ እርሱም ክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው፤ እርሱ በተናቀችው አህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ ይህም በእርሱ ዘንድ ከሥነፍጥረት የተናቀ እንደሌለ ያስረዳናል፡፡ ስለዚህም ከደሃ ቤተሰብ ተወለደ፡፡ ሌላውን ትርጉም መሠረታዊ ከሆነው ዋና ቁም ነገር ጋር ላለመደባለቅ ለጊዜው ትቼዋለሁ ፡፡
ጌታችን የድሃው ድህነት ይሰማዋል ፡፡ እንዲሰማውም ለመግለጽ ሲል ደሃ ሆነ ፡፡ ለእኛ መገልገያነት የተሰጠችን አህያይቱ የክርስቶስ የሰላሙ መገለጫ በመሆኑዋ ከከበረች እንዴት እግዚአብሔር አምላክ ለዘለዓለማዊ ማደሪያነት የመረጠው ሰው ፣ መመለኪያው ያደርገው ዘንድ ከፍጥረት ሁሉ አልቆ የፈጠረው ሰው የበለጠ አይከብር ? ስለዚህም ጌታችን ሰው ሁሉ በእርሱ ዘንድ እኩል እንደሆነ ፣ ሰውን ከሰውነቱ ይልቅ ልብሱን፣ ከነፍሱ ይልቅ ሰውነቱን፣ ተመልክተን የገዛ ወገናችንን እንዳንንቀው፣ ከነመኖሩም ዘንግተን እንዳንጥለው፣ ለማሳሰብ በምድራዊ ባለጠግነት ደሃ ከሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ ፡፡
ስለዚህም ጠጉሩን አለመቆረጡ በድህነት ምክንያት ይሆንን? እርሱ ያውቃል፡፡ ወይም ናዝራዊ የተባለበት ምክንያት ራሳቸውን ለእግዚአብሔር እንደቀደሱት ናዝራውያን ዓይነት አኗኗር ይኖራል ስለተባለለትም ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ ጌታችን በምድራዊ ብልጥግና ደሃ ከምትባለው ቅድስት ድንግል ማርያም ሥር አደገ፡፡ በምድራዊ ሀብት ድሆች ከተባሉት ወገን ስለተወለደ ደሃ የደረሰበት ሁሉ ደርሶበታል ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ይህንን እዚህ ላይ እናሳጥረውና ወደሌላ እንግባ፡፡ ስለምን ጌታችን ከድሃይቱ ጎጆ አደረ?
ወገኔ ሆይ! የክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመምጣቱ ዋናው ምክንያት ፍቅርን በማጥፋታችን ምድሪቱን ምን ያህል እንዳጎሳቆልናት በሕይወቱም በቃሉም ሊያስተምረን ፈልጎ አይደለምን? በእውነት እርስ በእርሳችን ፍቅር ቢኖረን ኖሮ ሥጋችን የሆነውን ወንድማችንን ፣ ደሃይቱን እኅታችንን ለአፍታ እንኳ ልንዘነጋት አይቻለንም ነበር ፡፡ እኛ እውነተኞች ወንድማማቾችና እኅትማማቾች ብንሆን የወገኖቻችን ውድቀት ያመናል፤ ሰቆቃቸው ይሰማናል፤ እዬዬአቸው ዋይ ዋይ ያሰኘናል፡፡ “ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው ወንድሙም የሚያስፈልገውን ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል?" ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት የለውም”(ዮሐ፫፥፲፫ -፳) እንዲል ከፍቅር ርቀን እየኖርን ነውና ደሃውን ዘነጋነው ግፋችንም በዛ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ፍቅር ከሌለን ወንድማችንን እኅታችንን እንጠላለን፤ የሚታየውን ወንድማችንን የምንጠላ ከሆነ እንዴት የማይታየውን እግዚአብሔርን ልንወደው እንችላለን?
ከክርስቶስ ልደት በፊት አስቀድመን የኖርንበት ሕይወት ይህን የመሰለ ነበር ፡፡ ከእግዚአብሔር ፍቅር በመራቃችን ሰውንም ከማፍቀር ራቅን ፡፡ በዚህም "ጉሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው"ተባለልን፤ ሙታን ሆነው ሙታንን የሚውጡትን ጣዖታትን መሰልናቸው፡፡ ነገር ግን አሁንም ከክርስቶስ ተምረን እንደሚጠበቅብን ሆነን መመላለስ ተስኖናል ፡፡ በእውኑ ድህነት በራሱዋ የኃጢአት ምክንያት እንዳልሆነች ፣ ደሃ በድህነቱ ምክንያት መናቅና መረሳት እንደሌለበት ፣ ፍቅር ልንሰጠው ልክ እንደ ክርስቶስ ቀርበን ልናውቀው ፣ በድህነት ሕይወት እንዳይኖርም ድህነት ከሚያመጣው የሰቆቃ ኑሮ ልናወጣው እንዲገባን ሊያስጠነቅቀን፣ ጌታችን ከደሃይቱ ጎጆ ማደሪያውን ያደረገ አይደለምን ?
“በእርሱ ሕይወት ነበረች”እንዲል ወንጌላዊው ሰው ያለ ክርስቶስ ሕይወት የለውም፡፡ አንድ ሰው በሕይወት መኖርን ከፈለገ ደግሞ አንገቱን ዝቅ አድርጎ ከደሃይቱ ጎጆ መግባት ሊጠበቅበት ነው ፡፡ ምክንያቱም ክርስቶስ በዚያ አለና ፡፡ ይህ ብቻ ግን አይደለም ፤ ደሃይቱን ወይም ደሃውን ከወደቀበት ሊያነሣው ይገባዋል ፡፡ በዚህ ጊዜ ክርስቶስ ስራብ አብልተኸኛል፤ ስጠማም አጠጥተኸኛል ይለዋል፡፡
ጌታችን እንዴት ርኅሩኅ ጌታ ነው !! ድሃውን ጎበኘነው ማለት ክርስቶስን ጎበኘነው ማለት እንደሆነ ሁሉ እኛም አስቀድመን በኃጢአት እጅግ ጎስቁለን፣ ፍጹም ማጣት ሠልጥኖብን፣ የጸጋው ድህነት ጎጆ ሠርቶብን፣ የነበርነውን ሰዎች ክርስቶስ ጎብኝቶን የእግዘአብሔር ልጅነት ሥልጣንንና በመንፈስ ቅዱስ ልዩ ልዩ ጸጋዎችን በመስጠት እጅግ ባለጠጎች አደረገን፤ እኛም ባለን መጠን ድሆችን በመጎብኘት ከድህነታቸው እንዲወጡ በማድረጋችን ምክንያት ክርስቶስን እንመስለዋለን ፡፡ እንዲህ ፈጸምን ማለት ጎብኚውም ተጎብኚውም ክርስቶስን መሰሉት ማለት ነው፡፡
ሰው በሰውነቱ ክቡር ፍጥረት ነው፡፡ በምድራዊ ሀብት እጅግ ባለጠጋ ብትሆን በክብር ከደሃው አትበልጥም፤ ደሃውም በድህነቱ ምክንያት በክርስቶስ በመመሰሉ ከባለጠጋው አይበልጥም፡፡ ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት እኩል ናቸው ፡፡ ባለጠጋው ባለጠጋ የሚባለው ክርስቶስን በልግስናው ሲመስለው ነው፡፡ ደሃውም ሰውነቱን ከኃጢአት ጠብቆ ሲገኝ ክርስቶስን ይመስለዋል ፡፡ ነገር ግን ደሃ ደሃ ሆኖ እንዲቀጥል የክርስቶስ ፈቃዱ አይደለም፡፡ ክርስቶስ በምድር ደሃ ሆኖ መመላለሱ አስቀድሜ እንደገለጥኩት ደሃው ክቡር ፍጥረት እንደሆነ ተገንዝበን እርሱን ከመናቅና ከመዘንጋት ፣ ፍቅርን ከመንሣት ተከልክለን ለደሃው ወገናችን ለክርስቶስ እንደምናደርግ ቆጥረን የሚያስፈልገውን አሟልተንለት በራሱ እንዲቆም ብሎም እርሱም በፈንታው ሌሎችን እንዲያቆም እንድናደርግ ለማሳሰብ በመፈለጉ ነው ፡፡
ደሃውም ባለጠጋውም ሁለቱም ለእግዚአብሔር አምላክ አገልጋይ ባሮች ናቸው፡፡ በባለጠጋው እጅ ያለው ምድራዊ ሃብት የእግዚአብሔር ነው ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ወደ ዓለም አንዳችም ይዘን አልመጣንምና አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም”(፩ጢሞ. ፪፥፯) እንዲል በእጃችን የያዝነው ሀብት የእርሱ የእግዚአብሔር ገንዘብ ነው፡፡ ከፍቅር ርቀን ዳግሞ ወደቀደመው ጎስቋላ ሕይወታችን እንዳንመለስ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡ “የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወድደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለኃጢአት መሥዋዕት አይቀርብልንምና የሚያስፈራ ነው ፤ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ ፡፡”(ዕብ.፲፥፳፮)ተብሎ እንደተጻፈው እንዳይሆንብን አስቀድመን ክርስቶስን እንወቀው ፡፡ ስለምን ከድሃ ቤተሰብ ተወለደ የሚለውም አስቀድመን እንረዳ በመቀጠል ፈቃዱን ለመፈጸም እንትጋ፡፡ በክርስቶስ ካልሆነ በቀር ሰዎችን ከቶ ማወቅም ሆነ ማፍቀር አይቻለንም ፡፡ ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን መስለን የእርሱን ምኞት ፈጻሚዎች እንድንሆን ያብቃን ፡፡ ለዘለዓለሙ አሜን
No comments:
Post a Comment