Monday, May 7, 2012

የአዳም እናትነት



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/08/2004
አምላኬ ሆይ አንተ ስለኢየሩሳሌም ጥፋት አዝነህ “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር ዶሮ ጫጩቶቹዋን ከክንፎቹዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ አልወደዳችሁምም”(ማቴ.23፡37) ብለህ በተናገርከው ኃይለ ቃል   የአዳምን እናትነት ልብ አልኩኝ፡፡
ጌታችን አዳምን ከምድር አፈር አበጅቶ የሕይወት አስትንፋስን እፍ አለበት፤ በዚህም ምክንያት አምላኩን መሰለ፡፡ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ በእርሱ አርአያና አምሳል ሔዋንን በማበጀት በአካል እንድትገለጥ አደረጋት፡፡ ከዚህም በኋላ ከእነርሱ የሚገኙ ሁሉ እነርሱን እንዲመስሉ እነርሱ ያላቸውን ሕይወት ሕይወታቸው አድርገው እንዲኖሩ በእነርሱና በዘሮቻቸው የልጅ ልጆቻቸውን ሁሉ ፈጠረ፡፡ እንዲህ በመሆኑም የአዳም ቅድስና ለእነርሱ ሕያውነት፤ የእርሱ ውድቀት ለእነርሱ ውድቀት ሆነ እንጂ ልክ እንደ መላእክት አንዱ ቢወድቅ ሌላው ጸንቶ በመቆም የሚድን አልሆነም፡፡ ስለዚህም አዳም ወደቀ እኛም የእርሱ የውድቀቱ ተጋሪዎች ሆንን፡፡ እግዚአብሔር በረድኤት ከአዳም ሲለይ ከእኛም በረድኤት ተለየ፡፡ ምንም እንኳ የአዳምና የሔዋን ኃጢአት ተባባሪዎች ባንሆንም የውድቀታቸው ተጋሪዎች ሆንን፡፡ ምክንያቱም በአዳም አንድ ሰው ሆነን ተፈጥረናልና፡፡