Tuesday, January 17, 2017

ፕሊሮማ

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
09/05/2009
ይህ ጽንሰ ሐሳብ ሰው ሁሉ በአዳም እንደሞተ በክርስቶስ ይድናል የሚለውን ነጥብ መሠረት ያደርጋል፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች እንደ አዲስ ግኝት ቆጥረው ቢያራግቡትም ጽንሰ ሐሳቡ እንደ ሐሳብ መነሣት የጀመረው 2ኛው /ዘመን በአርጌንስ ወይም በኦሪግን ነው፡፡ አርጌንስ ወይም ኦሪግን ፍጥረት ሁሉ ይድናል ብሎ የተነሣው  በጊዜው በፍልስፍና ውስጥ ተተብትበው የነበሩትን ለመመለስ ሲል ነበር፡፡ በእርግጥ ሰውም ይሁን ሰይጣን ለመዳን ፈቃደኛ ከሆነ እግዚአብሔር ሊያድናቸው ይችላል ቢሆንም ግን የገዛ ፈቃዳቸው ገድቦአቸው ከመዳን ርቀው ተገኝተው ነው እንጂ እግዚአብሔር እነርሱን ለማዳን ፈቃዱ ሳይኖረው ቀርቶ አይደለም።
ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ ግሪካውያንን ወደ ክርስትና ለመመለስ ሲል  “የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ። ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ።”(የሐዋ.1723) ማለቱን ልብ እንላለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ማለቱ ግሪካውያንን ለመመለስ ሲል እንጂ በአግባቡ ሳያውቁ የሚያመለኩት ክርስቶስን ነበር እያለ እንዳልሆነ ማንም ልብ ይለዋል፡፡ ነገር ግን እነርሱን ወደ ክርስትና ለማቅረብ እንደ መግቢያ በር ግን ተጠቅሞበታል፡፡ ይህ መንፈሳዊ ጥበብ ነው፡፡ ስለዚህም ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ ልንገራችሁ በማለት እነርሱን ወደ ክርስቶስ አምልኮ እንዳመጣቸው እንረዳለን፡፡ እንዲሁ በአርጌንስ ጊዜ ፍልስፍና ያለ ልክ ከፍ ከፍ ያለበት ጊዜ ስለነበረና እነርሱም የክርስቲያኖች አምላክ ጭካኝ ነው፤ አምላካቸው በአእምሮ ከእርሱ የሚያንሱትን በድለው ሲገኙ ሳይራራ ወደማይጠፋ ዘለዓለማዊ እሳት ይጨምራቸዋል የሚል አስተምህሮ አላቸው ብለው ክርስትናን ከመቀበል ተመልሰው ነበረና፡፡