Tuesday, January 17, 2017

ፕሊሮማ

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
09/05/2009
ይህ ጽንሰ ሐሳብ ሰው ሁሉ በአዳም እንደሞተ በክርስቶስ ይድናል የሚለውን ነጥብ መሠረት ያደርጋል፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች እንደ አዲስ ግኝት ቆጥረው ቢያራግቡትም ጽንሰ ሐሳቡ እንደ ሐሳብ መነሣት የጀመረው 2ኛው /ዘመን በአርጌንስ ወይም በኦሪግን ነው፡፡ አርጌንስ ወይም ኦሪግን ፍጥረት ሁሉ ይድናል ብሎ የተነሣው  በጊዜው በፍልስፍና ውስጥ ተተብትበው የነበሩትን ለመመለስ ሲል ነበር፡፡ በእርግጥ ሰውም ይሁን ሰይጣን ለመዳን ፈቃደኛ ከሆነ እግዚአብሔር ሊያድናቸው ይችላል ቢሆንም ግን የገዛ ፈቃዳቸው ገድቦአቸው ከመዳን ርቀው ተገኝተው ነው እንጂ እግዚአብሔር እነርሱን ለማዳን ፈቃዱ ሳይኖረው ቀርቶ አይደለም።
ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ ግሪካውያንን ወደ ክርስትና ለመመለስ ሲል  “የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ። ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ።”(የሐዋ.1723) ማለቱን ልብ እንላለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ማለቱ ግሪካውያንን ለመመለስ ሲል እንጂ በአግባቡ ሳያውቁ የሚያመለኩት ክርስቶስን ነበር እያለ እንዳልሆነ ማንም ልብ ይለዋል፡፡ ነገር ግን እነርሱን ወደ ክርስትና ለማቅረብ እንደ መግቢያ በር ግን ተጠቅሞበታል፡፡ ይህ መንፈሳዊ ጥበብ ነው፡፡ ስለዚህም ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ ልንገራችሁ በማለት እነርሱን ወደ ክርስቶስ አምልኮ እንዳመጣቸው እንረዳለን፡፡ እንዲሁ በአርጌንስ ጊዜ ፍልስፍና ያለ ልክ ከፍ ከፍ ያለበት ጊዜ ስለነበረና እነርሱም የክርስቲያኖች አምላክ ጭካኝ ነው፤ አምላካቸው በአእምሮ ከእርሱ የሚያንሱትን በድለው ሲገኙ ሳይራራ ወደማይጠፋ ዘለዓለማዊ እሳት ይጨምራቸዋል የሚል አስተምህሮ አላቸው ብለው ክርስትናን ከመቀበል ተመልሰው ነበረና፡፡

ስለዚህ እነርሱን ወደ ድኀነት ለማቅረብ ፍጥረት ሁሉ እንዲድን የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ የሰው ፈቃደኝነት ግን ወሳኝ እንደሆነ ሰብኮ እነርሱን ወደ ክርስትና መልሶአቸዋል፡፡ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ የእርሱ አስተምህሮ የአሁኑንም ያለፉትንም ዘመናት የሚዋጅ ሆኖ ስላልተገኘ ቤተ ክርስቲያን እንደ ራሷ አስተምህሮ አድርጋ አልተቀበለችውም፡፡  ሲቀጥል የኦሪግንን ወይም የአርጌንስን አስተምህሮ የሚመስል አስተምህሮ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ይዞ ተነስቶአል፡፡ ነገር ግን መሰለ እንጂ የቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ አስተምህሮ ፍጥረት ሁሉ ይድናል የሚል ድምዳሜ ያለው አልነበረም፡፡ የሚያጠነጥነውም በክርስቲያኖች ላይ ነው፡፡ በእርሱ አስተምህሮ የሰው ልጅ በግልም ሆነ በአንድነት የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ እንዳለ ይናገራል፡፡ አንዳንዶች ግን ይህን መሠረት አድርገው በብዙ ተሰናክለዋል፡፡ መነሻ ነጥቡምየእግዚአብሔር ሐሳብ በክርስቶስ ዓለሙን መጠቅለል ነው”(ቆላ.124) የሚለው የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ነው፡፡
እንደ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ አስተምህሮ እያንዳንዱ ነፍስ በየራሱ የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ያለው ሲሆን   በጋራም አንድ የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ አለው፡፡  እናም አንዲት ነፍስ ብቻዋንም የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ አላት፡፡ ከሌሎች ጋር  በክርስቶስ አንድ አካል ስትሆን የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ይኖራታል፡፡ እኛ በአዳም አንድ አካል ነበረን ከአዳም ሔዋን ተገኘች ከእነርሱ አንድነት እኛ ተገኘን ስለዚህ በአዳም አንድ አካል ነበረን፡፡ ይህም በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረ ነው፡፡ ከውድቀት በኋላ ደግሞ በክርስቶስ አንድ አካል ሆነን ዳግም በጥምቀት ተፈጠርን፡፡ በእርሱ አንድ አካል በመሆን ከቀድሞ በላቀ መልኩ የእግዚብሔር መልክና ምሳሌ በሙላት እንዲኖረን ሆኖአል ፡፡ ቃሉም እንዲህ ይነበባልሰው መጀመሪያ ሲፈጠር እንደነበረው እንዲሁ በዓለም ፍጻሜም እንዲሁ በክርስቶስ አንድ የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ይኖረዋልየሚል ነው፡፡
ይህም  በክርስቶስ ዳግም በተፈጠረ አንዱ ሰው የሚፈጸም ነው፡፡ ይህም የክርስቶስን ሥጋ መስሎ ዳግም በክርስቶስ በመፈጠሩ ነው፡፡   ይህ ግልጽ እንዲሆን በአዳም አንድ አካል እንደነበርን በክርስቶስ ደግሞ በመጨረሻው ፍርድ ሰዓት አንድ አካል እንደምንሆን ሲያስረዳ፡- “እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።” (ፊልጵ.321) ይለናል፡፡
ይህ መች ይፈጸማል? በትንሣኤ ነው፡፡ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው:- “አካል አንድ እንደሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደሆኑ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል።(1ቆሮ.1212-13) እንዲል ማለት ነው፤ ይህም በክርስቶስ አንድ አካል ሆነን በእርሱ አንደ አንድ ሰው መሆናችንን ያስረዳል፡፡ ስለዚህ ይህንን ነው እንግዲህ ሁሉ አቀፍ ሰብአዊነት(ፕሊሮማ) የሚባለው፡፡ ይህን ነው እንግዲህየእግዚአብሔር ሐሳብ ዓለሙን በክርስቶስ መጠቅለል ነውየሚለው ቃል ትርጉም፡፡ ይህ እንግዲሀ ሰው ሁሉ ይድናል የሚል ትርጉምን የሚሰጥ አይደለም፡፡
በዚህ የቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ቃል ሰው ሁሉ ይድናል የሚል ትንታኔ እንዳልሰጠ መረዳት እንችላለን፡፡ ሁሉ አቀፍ ድኅነት የሚፈጸመው በትንሣኤ በእርሱ ባመኑት ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ለብቻውም በአንድነትም የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ይኖረዋል፡፡ ይህ ፍጻሜን የሚያገኘው በምጽአት ነው፡፡ በምጽአት አስቀድመው የሞቱትም አሁን የሚኖሩትም ወደፊትም የሚኖሩትም በክርስቶስ አንድ አካል ይሆናሉ፡፡ በአጭሩ ሥጋችን የክርስቶስን ሥጋ እንዲመስል ይለወጣል፡፡ በዚህም መንገድም አንድ አካል ይሆናሉ፡፡ ለዚህም እንደ መረጃ የሚጠቀምባቸው ቆላ.1241ቆሮ.1227 እና ኤፌ.41215-16 ነው፡፡ እኒህ ሁሉ የሚያወሩት ሰው ሁሉ ይድናል የሚል ሳይሆን ነጻ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው ወደዚህ ሕብረት የመጡ ሁሉ እንደሚድኑ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment