በቀጥታ የተወሰደ
08/05/2009
መቼም የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት መጽሐፍን የቃላትን ትርጉም ሽቶ የማያነብ የለም ብዬ እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን መግቢያቸው ከመርዘሙ የተነሣ ትግሥእት ኖሮት የሚያነብ ጥቂቱ ነው ብዬ አምናለሁ ከእኔ ጨምሮ ማለት ነው፡፡ አንድ ወቅት እንዲሁ አለፍ አለፍ ብዬ የመዝገበ ቃላቱን መግቢያ ስመለከት ይህን ጽሑፍ አገኘሁት፡፡ ዛሬ ደግሞ ደግሜ አነበብሁት ይህ ጽሑፋቸው ምናልባት በጥንተ አብሶ ዙሪያ ያለውን የቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ግልጽ ሳያደርግልን አይቀርም በሚል አንባቢ እንዲያነበው ስል እነሆ ብያለሁ፡፡
“ፊደል ጥፈት ለአዳም ልጆች የተገለጡና የተሰጡ በአዳም ዕድሜ ነው ከዚያውም በሳብዓይ ምዕት በሣልሳይ ትውልድ በሄኖስ ዘመን እንደ ሆነ ታውቋል፡፡ የተሰጡበትም ምክንያት ይህ ነው፤ ሰው በግዜር ምሳሌ መፈጠሩ እንደ መላእክት ሕያው ኹኖ በሕገ ልቡና ሊኖር እንጂ በተፈጥሮ የተሰጠውን ሕግ ረስቶ ዘንግቶ እንደገና መጽሐፋዊ ሕግ ሊጥፍና ሊያስጥፍ ልቡናውን በመጽሐፍ ሊደግፍ ሕይወቱንም ዐጥቶ ሊቀበር ከመሬት ሊወተፍ እንደ ቅጠል ሊረግፍ አልነበረም፡፡(ይህ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የማቴዎስ ወንጌልን ሲተረጉም መግቢያ ላይ የተጠቀመበት አገላለጽ ነው፤ ይህ የሚያሳየው የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሥራን የኢትዮጵያ ሊቃውንት ወደ ግአዝ መልሰው ይጠቀሙበት እንደነበረ ነው) መጽሐፈ ኩፋሌ ሺሑን ዓመት ፩ ዕለት ብሎ አዳም ዕለቱን ተፈጥሮ ወዲያው በድሎ አንዲቱን ቀን እንኳ ሳይፈጽም ሞተ ይላል፤ ይኸውም ለሺሕ ፸ ዓመት ሲቀረው በ፱፻፴ ማለት ነው፡፡ ሺሑ ዓመት በግዜር ዘንድ ፩ ዕለት ሲባል አንዱ ሰዓት ደግሞ ሧ፩ ዓመት ከ፰ ወር ከ፫ ቀን ፮ ሰዓት ከ፪ ደቂቃ ከ፴(ሴኮንድ) ቅጽበት ይኾናል፡፡
አዳም የባሕርይ ጠላት የሌለበት መስሎ ዐርፎ ተዘልሎ በተድላ ሳለ የኅሊና ጽነት ኀጢአትና ሞት እነዚህ ሦስቱ የባሕርይ ሳይኾኑ ከባሕርይ ጋር እንደ ፈትልና እንደ ሠም እንደ ፀምርና እንደ ቀለም ተስማሚነት ስላላቸው ከአፍአ መጥተው ባሕርዩን እንደ ፈትል እንደ ፀምር ቀልመው አሳድፈው ንጣቱን ጥራቱን አጠፉበት፡፡ ርሱም እንደ መላእክት ነጻነትና የልጅነት ሥልጣን ስላለው ተስማሚን በርትዐት ጨቁኖ ከጽነትና ከኀጢአት ጋር መዋጋት መታገለ ተዋግቶና ታግሎም ማሸነፍ መጣል ምክረ ከይሲንም አለመስማት አለመቀበል ሲችል እግዜር በልቡናው ያዳፈነለትን እሳተ ሕግ ገላልጦ አንድዶ በመሞቅ ፈንታ አጥፍቶ ይርቅ ዘንድ እንደ ዲያብሎስ ጽድቅን ጠልቶ ዐመጻን ቢወድ ውዱና ፈቃዱ ጽነትን ጽነት ኀጢአትን ኀጢአት ሞትን ከርግማን ጋር ስበው ተሳስበው ተባብረው ተጫፍረው መጡበት፡፡ የባሕርይ አለመኆናቸው ሊታወቅ ፯ ዓመት ሙሉ በገንት ሲኖር የኀልዮና የነበብ የገቢር ኀጢእት አልተገኘበትም፡፡ እስከ ሺሕ ዓመት ግን እንደዚሁ በጽድቅና በንጽሐ ጠባይዕ ጸንቶ ቢኾን ብልየትና ሞት ሳያገኙት ረቆ ታድሶ በግዘፉ ፈንታ ርቀትን ለብሶ ሺሕ ዓመት ያልሞሉ ልጆቹ እያዩት ከዓለመ ሥጋ ወደ ዓለመ ነፍስ ሊያግ ነበር፤ ዳግማይ አዳም የተባለው ልጁ በትንሣኤ ረቆ ታድሶ ወንድሞቹ እያዩት እንዳረገ፡፡ (ይህ ለእርሱ መታደስ አስፈልጎት ሳይሆን አባቶች "በሰው ሥርዓት" ብለው እንዲተረጉሙ በእርሱ ትንሣኤ እኛ መታደስና መርቀቅን እንዳገኘን ለማስረዳት ነው እንጂ ርሱስ ከትንሣኤ በፊትም በኋላም ያው ነው ሁሉን በፈቃዱ አደረገው)
እንዲህ በተፈጥሮ ንጽሕና ጽሩይ ምዑዝና ጥዑም የነበረ የሰው ምንጭ አዳም ከ፯ ዓመት በኋላ ፍትወታት እኩያት ኀጣውዕ ተሰብስበው ገብተው ሲዋኙበት ምድራዊነቱ ተናውጦ ሰማያዊነቱም ተበጥብጦ ንጽሐ ጠባየዑ ስላደፈና ስለደፈረሰ በዘር በሩካቤ ከርሱ እየተቀዳ ሞትና መቃብር ሳያቋርጡ የሚጠጡት ምድራዊ ሰው ኹሉ በፈሳሽነቱ እየተላና እየጎሸ እየሻገተና እየገማ አየተበላሸ ኼደ፡፡ ምድር አፍ አውጥታ እስክትከሰውና እስክትፋረደው ሰማይም ምደርን በንፍር ውሃ እስኪጠብሰውና እስኪያነደው ዳኛውም እግዚር ሰውን በመፍጠሩ ዐዝኖ ተጠጥቶ ያንድ ሰው ዘር ብቻ አስቀርቶ ኹሉን በማየ አይኅ እስኪያጠፋው ድረስ ከመባስ በቀር መመለስ አልቻለም፡፡
በሄኖስም ዘመን ከነበሩ ሰዎች ደቂቀ ሴት ብቻ ከናባታቸው ሲቀሩ የቃየልና የወንድሞቹ ዘር ልጁም ዐዋቂውም ተጨልጠውና ተገርኝተው ወዳምልኮ ጣዖት ስለ ኼዱ ክፋታቸውም በብዛታቸው ልክ ስለኾነ የማየ ዓይኅን እስኩታህ ገፈታ ቀምሰዋል ማየ ግዮን እንደ ጭፍራ ታዞ ከሰውም ከከብትም ሢሶ ሢሦውን አጥፍቶአል፤ ምድርም ቀድሞ በአዳም እንደ ተረገመች የዘሩባትን ዘር ቆርጥማ ያልዘሩባትን ሦክና አሜካላ ደንደር ኰሸሽላ ዶቢና ሻማ ኵርንችት ዐቃቅማ አበቀለች ይህም ኹኖ ባሱ እንጂ አልተመለሱም፡፡……
ኀጢአት ከባሕርያችን ናት ለሚሉም አለመኾኗን ሲያጠይቅ መሐልኩ ለክሙ ኃጥአን ከመ ኢኮነ ደብር ገብረ ወኢይከውን ወኢወግር አመተ ለብእሲት ከማሁ ኀጢአትኒ ኢተፈነወት ዲበ ምድር፤ አላ ሰብእ እምርእሶሙ ፈጠርዋ፤ ወለመርገም ዐቢይ ይከውኑ እለ ገብርዋ ብሎባቸዋል፡፡
ሐተታ
የአዳም ኀጢአት ከአባት ወደ ልጅ መውረዱ አዳምን መስለው ተከትለው በሚሠሩት ብቻ ነው እንጂ በማይሠሩትና በሚነቅፉት እንደ ሔኖክ በሚጸየፉት በልጆቹ ኹሉ አይደለም ይኸውም ቡርክት አንቲ እምአንስት ወብሩክ ፍሬ ከርሥኪ በተባሉት እናትና ልጁ ይታወቃል፡፡ ጽድቁም እንደ ኀጢአት ነው ከባሕርይ ተከፍሎ በመወለድ አይወረስም አባትን መስሎ በመሥራት ብቻ እንጂ(ሕዝ.፲፪፡፬ እና ፳ )፡፡ በዘርም እንዳይወርድ የአዳም ኃጢአት የነፍስ ነው እንጂ የሥጋ አይደለም ነፍስም እንደ አዳም ነፍስ ከፈጣሪ እፍታ ንጽሐ ጠበይዕ ተገኝታ ከአባት ከእናት በተከፈለው በዘርና በደም ታድራለች እንጂ ርሷአትከፈልም(ኢሳ.ሧ፪፡፭ ዘካ.፲፪፡፩)፡፡ ወእንዘ ማይ ውእቱ ታረግዐ በጥበብከ ወትነፍኀ ላዕሌሁ መንፈሰ ሕይወት፡፡ ወእምአሐቲ መዝገብ ዘእምእስትንፋሰ አፈሁ ይሠርጻ ወያሕመለምላ ነፍሳት እለ ይትወለዳ እምዝንቱ ዓለም እንዳለ(ቅዳ፡አት፡ግሩ)…..እያለ ይቀጥላል የቀረውን እናንተ አንብቡት፡፡
ከዚህ ምን እንረዳለን ኀጢአት ከአባትና ከእናት እንደማወርድና እንደማይወረስ አይደለምን? እኔም እንዲሁ ብዬ አምናለሁ ከእኔ ጨምሮ ማለት ነው፡፡
This comment has been removed by the author.
ReplyDeletehttps://kidanewoldkifle.blogspot.com/
ReplyDelete