Sunday, January 15, 2017

በእውነት ብፅዕት


ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
7/5/2009

ያቺ ቅድስት ብላቴና ንጉሥ እልፍኙ ያደርጋት ዘንድ ሳይፈጥራት ያወቃት፥ ከማኅፀን ሳይሠራት እናቱ ትሆን ዘንድ የነፍሷን ውበት ተመልክቶ የወዳዳት፥ ቤተ መቅደሱ በመሆን የእንስሳት መሥዋዕት የሚሠዋበትን የኦሪቱን ቤተ መቅድስ ልታሳልፍ የ"ቃል" ቤተ መቅድሱ ለመሆን ተመረጠች። በመንፈስ ቅዱስ የከበረች፥ አብ ልጁን ጸንሳ ትወልድ ዘንድ የሚያጸናት ፥ ራሱን ቤተመቅደስ ላለው ቃል ቤተ መቅድሱ ለመሆን የታጨች፥ ወላጅነትን ከአብ ጋር ለመጋራት የተመረጠች፥ መንፈሷ በመንፈስ ቅዱስ በሆነ ደስታ የተሞላ፥ ነፍሷ በአምላኳና በመድኅኒቷ ሐሴት የምታደርግ ፥ በሲኦል ላሉ ነፍሳት  በምድር ላሉ ሙታን የመዳናቸው ተስፋ የነበረችና ናፍቆታቸው የሆነች በእናቷ ሃና እጅ እርጅና ወደ ደቆሳት ቤተመቅድስ ገባች።

ያን ጊዜ የነቢያትን ቦታ ይዘው ሰማያውያንና ምድራውያን አንድ እንደሚሆኑ ሲስብኩ የነበሩ በቤተ መቅድሱ ውስጥ የተቀረጹ የኪሩቤል ምስሎች አገልግሎታቸውን ፈጽመው በቅዱሳን መላእክቱ ሲተኩ ፥ አማናዊቷ ታቦት ወደ ቤተመቅደሱ ስትግባ፥ ራሱን ቤተመቅደስ አካሉን ቅድስት ያለው ጌታችን ቤተመቅደስ ባደረገው ሰውነቱ ራሱን መሥዋዕት አቅራቢ ሊቀ ካህናት አድርጎ ራሱ መሥዋዕትና ራሱ መሥዋዕት ተቀባይ በመሆን በሥርየት መክደኛው መስቀል ላይ ራሱን ሊያቀርብ  የወደደ ከአንቺ ይወለድ ዘንድ ከላይ ከአርያም ወዳንቺ መጣ።
ድንግል ሆይ አንቺ የአብርሃም ተስፋ የሆነውን ተስፋ በማደረግ ንጽሕን ተላብሰሽ፥ ቅንነትን ታጥቀሽ፥ ጭምትነትን ተጫምተሽ ፥ ልብሽ ከአምላክሽ ጋር የአምላክሽም ልብ ከአንቺ ጋር ሆኖ ትኖሪ ነበር።  ሁሌም ከእግዚአብሔር ጋር ነበርሽ፥ ጸጋሽም እርሱ ነበር። እርሱ እኛን ከነነውራችን የወደደን ጌታ በጸጋ የተሞላሽ ትሆኙ ዘንድ በነፍስሽ ያደረ፥ ከሥጋሽ ሥጋን ከነፍስሽ ነፍስን ነስቶ ይወለድ ዘንድ የመረጠሽ ድንግል ሆይ! አንቺ በአብ ዘንድ የነበረሽ መወደድና አንቺን የመፍጠሩ ምክንያት እንዴት ታላቅ ነበር??  ስለዚህ ነው ይህን በመንፈስ ቅዱስ በመረዳት "እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ብጽዕት ይሉኛል"ምክያቱም "እግዚአብሔር በእኔ ታላቅ ሥራን አድርጓልና" ብለሽ በታልቅ ድምጽ  ጮኸሽ መናገርሽ።
ስሙ እውነት የሆነ እርሱ ስለእውነት ሊነግረን፥ የዳዊትን ዙፋን ለዘለዓለም ሊያጸና፥ ርግማናችንን ሊሽር፥ ሰላምን ሊያመጣ፥ በመስቀሉ ላይ ሊነግሥ፥ እርቅን ሊፈጥር፥ ፍቅርን ሊያጸና፥ ሰማይን ምድር ምድርን ሰማይ ሊያደርግ አምላክ ወሰብእ ሆኖ  ከአንቺ ተወለደ። ይህ በእውነት ታላቅ ሥራ ነው። ስለዚህ ድንግል ሆይ  እውነት ብጽዕት እንልሻለን ምክንያቱም እግዚአብሔር በአንቺ  ታላቅ ሥራን ሠርቶአልና።

No comments:

Post a Comment