Thursday, May 7, 2020

አማልክት ከምድር ሲወጡ አየን


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/08/2012
አዲስ አበባ
አምላኬ ሆይ ዛሬ ለጸሎቴ መልስን ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ አውቃለሁ አንተ ርኅሩኅ አምላክ ነህ እንደ ፈቃድህ የሆነን ጸሎት የሚያቀርብን ሰው ትሰማዋለህ፡፡ ነገር ግን ጌታ ሆይ ዛሬ ምሽቱን በምንጣፌ ላይ ዕንቅልፍ ሳይጥለኝ ግን ጋደም ብዬ ወደ መቃብር ሥጋህ መውረዱን አሰብሁ፡፡ ነፍስ ከሥጋ መቃብር ከገባች ፈጥና ትወጣለች እንጂ ከእርሱ ጋር ምድራዊው መቃብር ውስጥ አትገባም፡፡ እንዲያ ቢሆን ግን ሰው ከነሕይወቱ ተቀብሮአል ይባላል እንጂ ነፍስ ወደ መቃብር ወረደች አትባልም፡፡ እንዲያም ቢሆን ሥጋ በነፍስ ኃይል በምድር ልብ ውስጥ መተንፈስ አትችልምና ነፍስ ፈጥና ሥጋን ትለያታለች፡፡ ነፍስም በዝግ መቃብር ሥጋን ተለይታ በአዳም ላይ የተፈረደውን ፍርድ ተቀብላ ወደ ሲኦል ትወርዳለች፡፡ እንዲህ ስል ከክርስቶስ ትንሣኤ በፊት ያለውን ጊዜ መናገሬ ነው፡፡  ጌታችን ግን ነፍሱን ከሥጋው በፈቃዱ ከለያት በኋላ በነፍሱ ወደ ሲኦል ወረደ፡፡ በምድር በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ በግዘፍ ሥጋ ለፍጥረት ሁሉ እንደተገለጠ በነፍሱም ወደ ሲኦል በመውረድ በመጠነ ነፍስ በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ሁሉ ተገለጠ፡፡  “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ብሎ በጌትነቱ ታያቸው፤ ነፍሳት ሁሉ በእርሱ አርአያና አምሳል ተፈጥረዋልና ጌታቸውን ለዩት “ከመንፈስህ ጋራ ብለው” እንደ ዮሐንስ መጥምቅ በደስታ ሰገዱለት፡፡ እነርሱም በቀኝ በኩል ከተሰቀለው ወንበዴ ጋር ወደ ገነት ከጌታ ጋር ገቡ፡፡

Monday, April 20, 2020

የልቡና ትንሣኤ - ወደ ነፍስ ትንሣኤ - የነፍስ ትንሣኤ - ወደ ሥጋና ለነፍስ ትንሣኤ

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
12/08/2012
የልቡና ትንሣኤ ስለ እርሱ ማወቅን፣ መረዳትን፣ ማመንንና መቀበልን ይጠይቃል፡፡ ይህም ማለት ከውኃና ከመንፈስ ተወልጄ የእግዚአብሔር ልጅነትን አግኝቻለሁ፤ አሁን የምኖረው ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣው ከክርስቶስ ጋር በተዋሕዶ ነው፤ አሁን ከሰማያውያን ጋር ኅብረትን ፈጥሬአለሁ፤ ከአእላፍት ቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳት ነፍሳት ጋር አንድ ጉባኤ  ሆኜአለሁ፤ ምንም እንኳ በምድር ብኖር በሰማያዊ ሥፍራ ነኝ ብሎ ማወቅ፣ መረዳት፣ ማመን፣ መቀበል ማለት ነው፡፡ ይህን ማወቁ፣ መረዳቱ፣ ማመኑና መቀበሉ ከሌለን ባልታደሰው በቀበርነው በአሮጌው ማንነታችን ዕውር ድንብራችንን መጓዛችን እንቀጥላለን፡፡ ያኔ የሥጋ ሞት ያስፈራናል፣ ዕለታዊው ነገር ያስጨንቀናል፣ ዘለዓለም የምኖር ይመስለናል፣ በመብል በመጠጥ ደስታን ለማግኘት እንተጋለን፣ የእግዚአብሔርን ሕልውና ትርክት ይመስለናል እንጂ አናምንበትም፡፡ እነዚህ የልቡናን ትንሣኤ በማጣታችን በእኛ ላይ የሚሰለጥኑብን ናቸው፡፡ ነገር ግን የልቡናን ትንሣኤ ገንዘብ ስናደርግ ያለፈው የጨለማ ጉዞ፣ ያለማወቅ ጉዞ፣ የሥጋ ባርነት ጉዞአችን ሁሉ ትዝ እያሉን ይቆጩናል፡፡ ከፊት ለፊታችን ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀን እንረዳለን፡፡ ገና መድረስ ካለብን ከፍታና መረዳት እንዳልደረስን፣ ሥጋችን የክርስቶስ ሥጋ ሆኖ በጥምቀት መለወጡን እንዳልተረዳነው ወደዚህም መረዳት ለመድረስ መትጋት እንዳለብን፣ ሕሊናችን ሁሌም ይህን  አሮጌውን ሰዋችንን ማለትም እንደ ሥጋ ፈቃድ መመላለሳችንን ገፍፈን እንደ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ እንድንመላለስ እንዲያተጋን ማሳሰብን ገንዘብ እናደርጋለን፣ የክርስቶስ አካል የሆነውን ሥጋችንን ባሕርይ ለማወቅ እንተጋለን፡፡ በአጠቃላይ ወደ ነፍስ ትንሣኤ እንመጣለን፡፡

Wednesday, February 12, 2020

ቀለማት በቤተ ክርስቲያን


ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
04/06/2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ
መዝሙረኛው ዳዊት፡- “ለእግዚአብሔር ምድር በምልዓ ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉእንዲል ለእግዚአብሔር ከፍጥረት ወገን የእርሱ ያልሆኑና ያለምክንያት የፈጠራቸው ፍጥረታት ከቶ ማግኘት አይቻልም፡፡ እርሱ በተለይ ለሰው ልጅ የእርሱ የሆነውን ከብር እንዲያው በከንቱ ሰጠው፡፡ ለእግዚአብሔር መገዛት፣ እግዚአብሔርን ማሰብ፣ እንደ መላእክትና እንደ ቅዱሳኖቹ የእርሱን ክብር ለማየት መናፈቅ ፖለቲካ አይደለም ወዳጆቼ፡፡ ፖለቲካም ከሆነ በእርሱ ሥር ሆኖ መኖር ለእርሱም መገዛት ከምንም በላይ ተመራጭ ነው፡፡ የእግዚአብሔር የሆነውንም መጠቀም ቢያስከብር እንጂ የሚያዋርድ አይደለም፡፡ ይልቅ የእርሱን ክብር ያውም አምላክ የሚከብርበትን የራሳቸው ሊያደርጉ የሚቋምጡ ግብረ ሰዶማውያን ይፈሩ እንጂ እኛስ እንደ ቅዱሳን መላእክትና ቅዱሳን ነፍሳት የእርሱን ከብር በታች በምድር በላይ በሰማይ ማየትን እንናፍቃለን፡፡ ይህን ክብሩንም ስንመገብ እንኖር ዘንድ ተጠርተናል፡፡