በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/08/2012
አዲስ አበባ
አምላኬ ሆይ ዛሬ ለጸሎቴ መልስን
ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ አውቃለሁ አንተ ርኅሩኅ አምላክ ነህ እንደ ፈቃድህ የሆነን ጸሎት የሚያቀርብን ሰው ትሰማዋለህ፡፡ ነገር
ግን ጌታ ሆይ ዛሬ ምሽቱን በምንጣፌ ላይ ዕንቅልፍ ሳይጥለኝ ግን ጋደም ብዬ ወደ መቃብር ሥጋህ መውረዱን አሰብሁ፡፡ ነፍስ ከሥጋ
መቃብር ከገባች ፈጥና ትወጣለች እንጂ ከእርሱ ጋር ምድራዊው መቃብር ውስጥ አትገባም፡፡ እንዲያ ቢሆን ግን ሰው ከነሕይወቱ ተቀብሮአል
ይባላል እንጂ ነፍስ ወደ መቃብር ወረደች አትባልም፡፡ እንዲያም ቢሆን ሥጋ በነፍስ ኃይል በምድር ልብ ውስጥ መተንፈስ አትችልምና ነፍስ ፈጥና ሥጋን ትለያታለች፡፡
ነፍስም በዝግ መቃብር ሥጋን ተለይታ በአዳም ላይ የተፈረደውን ፍርድ ተቀብላ ወደ ሲኦል ትወርዳለች፡፡ እንዲህ ስል ከክርስቶስ ትንሣኤ
በፊት ያለውን ጊዜ መናገሬ ነው፡፡ ጌታችን ግን ነፍሱን ከሥጋው በፈቃዱ
ከለያት በኋላ በነፍሱ ወደ ሲኦል ወረደ፡፡ በምድር በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ በግዘፍ ሥጋ ለፍጥረት ሁሉ እንደተገለጠ
በነፍሱም ወደ ሲኦል በመውረድ በመጠነ ነፍስ በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ሁሉ ተገለጠ፡፡ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ብሎ በጌትነቱ ታያቸው፤ ነፍሳት ሁሉ በእርሱ አርአያና
አምሳል ተፈጥረዋልና ጌታቸውን ለዩት “ከመንፈስህ ጋራ ብለው” እንደ ዮሐንስ መጥምቅ በደስታ ሰገዱለት፡፡ እነርሱም በቀኝ በኩል
ከተሰቀለው ወንበዴ ጋር ወደ ገነት ከጌታ ጋር ገቡ፡፡
ይህ ቁምነገር የሳኦልንና የሳሙኤልን ታሪክ አስታወሰኝ፡፡ ይህን ታሪክ
ስናገረው እኛም ሳኦልን መስለነዋልና በእጅጉ በማዘን ነው፡፡ ምክንያቱም ቢያንስ ከሳኦል እንኳ የተሻልን መሆን ተስኖናልና፡፡ ታሪኩ
ከብዙ ባጭሩ እንዲህ ነው፡- እግዚአብሔር አምላክ ሳኦልን ከእርሱ ያገኘውን ሥልጣንና ኃይል የራሱ አድርጎ በመታመኑ ምክንያት “እስቲ
ከእኔ ውጭ እኔ የሰጠኹህ ሥልጣንና ኃይል ያገለግልህ እንደሆነ ልይህ ” ብሎ ለፍልስጤማውያን አሳልፎ ሰጠው፡፡ እርሱም በፍልስጤማውያን
ፊት ደካማ መሆኑን ሲያምን አምላኩን ፈለገ፤ አምላክ በኡሚምና በቱሚም፣ በራእይ፣ ወይም በነቢያት መልስ እስኪሰጠው ድረስ ጠበቀ፡፡
ጠበቀ እንጂ መልስ አላገኘም፡፡ እግዚአብሔር ዝም አለው፡፡ በልቡም “በል የሰጠኹ ስልጣን ወይም ኃይል ያድንህ እንደሆነ እንይ”
አለው፡፡ ሳኦል ከአምላክ ያገኘው ሥልጣንም ሆነ ኃይል ወይም ንብረት ወይም ሌላ ነገር እርሱ ባለቤቱ ካልተጨመረበት ከንቱ፣ ባዶ፣
አንዳች የማይፈይድ፣ የማይታደግ መሆኑን አልተረዳም ነበር፡፡
እኛ ግን በዘመናት ሁሉ ይህን ሳንማር ኖረናልና አሁንም እንደ ሳኦል
በራሳችን ታምነን አምላክ ከእኛ እንዲለይ እየጠየቅነው ነው፡፡ እንዴት ቢሉ እርሱን ሳንይዝ ራሳችንን ከሞት የምናድን መስሎን ከእርሱ
ባገኘነው ሥልጣን፣ ጥበብና ኃይል ተመክተናልና፡፡ እርሱ ግን ቸር ነው በእርሱ ፊት ራሳቸውን ስላዋረዱ ቅዱሳኑ ብሎ ታግሦናል፡፡
በቁጣው ሌሎች ላይ እንዳደረገው አልፈጸመብንም፡፡ አሁንም ግን ከእርሱ ጋር ሆነን ሁሉን ማሸነፍ እንደምንችል አውቀን እንዳላዋቂ
ሆነን ሥልጣኔ፣ ኃይሌ፣ ጥበቤ በምንለው ታምነን እየተሸነፍን ነው፡፡ መሸነፋችንን ስንረዳው ደግሞ አምላክን ወደ መለማመጥ እንመጣለን
ልክ እንደ ሳኦል ማለት ነው፡፡ በእውኑ በራሱ እንደታመነ እንደ ሳኦል ሥልጣኔ፣ ጥበቤ፣ መድኀኒቴ መከላከያዬ ወዘተ የምንለው እግዚአብሔር
“እስቲ የታመኑባቸውና ከእኔ ያገኟቸው እነዚህ ነገሮች ካለእኔ ያድኗቸው እንደሆነ እንይ” ብሎ ዝም ቢለን ምን ይውጠናል?
ወደ ቀደመው ነገሬ ልመለስ ሳኦል እግዚአብሔር አምላክ በኡሚም ቱሚም፣
በራእይ፣ በነቢያት አላናግር ሲለው ርኩሳት መናፍስትን ወደምትጠራዋ ሴት አመራ፡፡ እባክሽ ሳሙአልን አንሽልኝ አላት፡፡ እርሷ ግን
መናፍስት ጠሪዎችን ያጠፋው ሳኦል ቢያገኘኝስ ብላ ፈራች፡፡ መናፍስትን የምትለየዋ ሴት አጠገቡዋ ያለውን ሳኦልን አለማወቋ ይገርማል!
የእግዚአብሔር ሰው ግን እንዲህ አይደለም፡፡ እዚህ ቦታ ላይ አንድ ታሪክ ልጨምርላችሁ፡- በእስራኤል ታሪክ እስራኤልን ለሁለት የከፈላት
ኢዮርብዓም የሚባለው ሰው ነበር፡፡ እርሱም በይሁዳ ነግሦ በሮብዓ ላይ በማመጽ ዐሥሩን ነገድ ለይቶ ወደ ጣዖት አምልኮ የመለሳቸው
የጥጃውን ምስል ዳግም በእስራኤል ምድር ያስመለከ ራሱን ንጉሥ አድርጎ የቀባ ሰው ነበር፡፡ ብዙ ክፋቶችን ፈጸመ ሕዝቡን ከእግዚአብሔር
አራቀ፡፡ አንድ ወቅት ልጁ አብያ በጽኑ ይታመምበታል፡፡ ያኔ ሚስቱን “ልብስሽን ለውጪና ወደ ሴሎ ሂጂ እነሆ በዚያ ሕዝብ ላይ የነገረኝ
ነቢዩ አኪያ በዚያ አለ፡፡ በእጅሽም ዐሥር እንጀራና አንጎቻዎች አንድም ምንቸት ማር ይዘሽ ወደ እርሱ ይዘሽ ሂጂ በልጁም የሚሆነውን
ይነግርሻል አላት፡፡ የኢዮርብዓምም ሚስት እንዲሁ አደረገች ተነሥታም ወሰ ሴሎ ሄደች፤ አኪያም ቤት መጣች፤ አኪያም ስለ መሸምገሉ
ዓይኖቹ ፈዝዘው ነበርና ማየት አይችልም፡፡ እግዚአብሔርም አኪያን፡- እነሆ ስለ ታመመው ልጅዋ ትጠይቅህ ዘንድ የኢዮርብዓም ሚስት
ትመጣለች ሌላ ሴትም መስላ ተሰውራለችና በገባች ጊዜ እንዲህና እንዲህ በላት አለው፡፡ እርሷም በደጅ ስትገባ አኪያ የእግሯን ኮቴ
ሰማ እንዲህም አለ፡- የኢዮርብዓም ሚስት ሆይ ግቢ ስለምንስ ሌላ ሴት መሰልሽ? እኔም ብርቱ ወሬ ይዤ ተልኬልሻለሁ፡፡ ሂጂ ለኢዮርብዓምም
እንዲህ በዪው፡- የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ከሕዝብ መካከል ለይቼ ከፍ አድርጌህ ነበር በሕዝቤም በእስራኤል
ላይ አለቃ አድርጌህ ነበር፤ ከዳዊትም ቤት መንግሥቱን ቀድጄ ሰጥቼህ ነበር፤ ነገር ግን በፍጹም ልቡ እንደተከተለኝ በፊቴም ቅን
ነገር ብቻ እንዳደረገ ትእዛዜንም እንደጠበቀ እንደባሪዬ ዳዊት አልሆንህም፡፡” በማለት ወቀሳውን ካቀረበ በኋላ “እንግዲህ ወደ ቤትሽ
ሂጂ እግርሽም ወደ ከተማ በገባ ጊዜ ልጁ ይሞታል፡፡ እስራኤልም ሁሉ ያለቅሱለታል፥ ይቀብሩትማል በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር
ዘንድ በኢዮርብዓም ቤት በዚህ ልጅ መልካም ነገር ተገኝቶበታልና ከኢዮርብዓም እርሱ ብቻ ይቀበራል።” ብሎ ነገራት፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ሰው አኪያ የኢዮሮብዓም ሚስት
ምንም ራሷን ለውጣ በእርሱ ፊት ብትቀርብም እግዚአብሔር ገልጦለት አውቋታል፡፡ ይህች መናፍስት ጠሪ ግን እርሷን የሚያናግረውን ሳኦልን
መለየት አልተቻላትም፡፡ በዚህም ነፍሳትን ካሉበት ከሲኦል ወኅኒ ቤት
ልታወጣ ይቅርና አጠገቧ እየሆነ ያለውን የማታውቅ ደካማ እንደሆነች ታወቀ፡፡ ቢሆንም እግዚአብሔር አምላክ የትንሣኤውን ምሥጢር ያሳየን
ዘንድ ሳሙኤልን ያች መናፍስት ጠሪ እያየች ከሲኦል አወጣው፡፡ በዚህም ምክንያት “አማልክት ከምድር ሲወጡ አየሁ” ብላ ጮኻ ተናገረች፡፡
ሳኦልም “መልኩ
ምን ዓይነት ነው? አላት። እርስዋም፦ ሽማግሌ ሰው ወጣ፤ መጐናጸፊያም ተጐናጽፎአል” አለች። ይህች መናፍስት ጠሪ አማልክት ስትል
“በእኔ ላይ ጌቶች የሆኑት ሳሙኤልንም
ጨምሮ ሲወጡ አየው” ማለቷ ነው፡፡ ይህ ምንን ያስረዳናል? ጌታችን ስለ ዳዊት ሲናገር “እንግዲያው ልጁ ከሆነ እንዴት ጌታዬ ብሎ
ይጠራዋል?” ብሎ ጸሐፈት ፈሪሳውያንን ጠይቆ አልነበረምን? ጌታችንስ እኔ ልጁ ብቻ ሳልሆን ጌታውም ነኝ ሲል እንዲህ ያለ አይደለምን?
ስለዚህ ጌታችን ለዳዊት ጌታው ነውና ዳዊት በጌታችን ላይ አንዳች ሥልጣን የለውም፡፡ ጌታችን ግን በእርሱ ላይ ሙሉ ሥልጣን አለው፡፡
በዚህም ሥፍራ በዚህች መናፍስት ጠሪ አማልክት የተባሉት ሳሙኤልንም ጨምሮ በእርሷ ላይ ሥልጣን አላቸው እንጂ በእነርሱ ላይ እርሷ
አንዳችም ስልጣን የላትም፡፡
ቢሆንም ሳኦል ዳዊት “የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔርም
ከሁሉ ያድናቸዋል። እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ
ይጠብቃል” እንዲሁም “እግዚአብሔርን የምትወዱ፥ ክፋትን ጥሉ፤ እግዚአብሔር የቅዱሳኑን ነፍሶች ይጠብቃል” እንዲል እግዚአብሔር ከቅዱሳን እንዳይለይ ሳዖል ያውቃልና፤ ስለታያት ሰው ገጽታ ብቻ ለይቶ ጠየቃት፡፡ ነገር ግን በጊዜው የሳሙኤል ነፍስ
ወደ ሲኦል ተመልሳ ወርዳለች እንጂ ትንሣኤ አልተፈጸመላትም፡፡ ቢሆንም በሰማይም በምድርም ምሉዕ የሆነ እግዚአብሔር በሲኦል ሳለች
ይጠብቃት ነበር፡፡ ጌታችን መድኅናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በነፍሱ ወደ ሲኦል በመውረድ ነፍሳትን ማርኮ ወደ ገነት አገባቸው፡፡
በዚህም አማልክት ከምድር ሲወጡ አየሁ እንዳለች በእውነት አማልክት ከምድር ወጥተው ወደ ገነት ሲገቡ በእምነት ተመለከትን፡፡ የነፍሳት
ትንሣኤ እንግዲህ ይህን ይመስላል፡፡ ወደ ገነት ያገባቸው በነፍስ ባሕርይ እነርሱን መስሎና አህሎ በሲኦል የተገኘው ጌታችን መዳኀኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በዚህም የሳሙኤልን ነፍስ ከሲኦል ያወጣና ከእርሱ ጋር የነበረ እግዚአብሔር አብና መንፈስ ቅዱስ እንደሆኑ
በዚህ የተረጋገጠ ሆነ፡፡ ወንጌል ስለጌታችን ትንሣኤ “ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ
የለም።” በማለት በገዛ ሥልጣኑ እንደተነሣ በራሱ ስልጣን ራሱን ማስነሣቱን ሲገልጥ “እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ
አስነሣው” እንዲሁም “ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር
ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም።” በማለትም
የአብን በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ ያለውን ተሳትፎ ገልጾልናል፡፡ “ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ
በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።” በሚለው ደግሞ የመንፈስ ቅዱስን ተሳትፎ እናስተውላለን፡፡ እርሱ ሲነሣ ነፍሳትን
ከእርሱ ጋር ከሲኦል በማውጣት በመሆኑም በእርግጥ አማልክት ከምድር
ሲወጡ አየሁ ማለታችን የተገባ ነው፡፡ በጌታ ልደት አብም መንፈስ
ቅዱስም ተሳትፎ እንደነበራቸው በትንሣኤውም የሆነው እንዲሁ ነው፡፡ ለዚያች መናፍስት ጠሪም ሥላሴ ለአብርሃም በሚታይ አካል እንደተገለጡለት ለእርስዋም የተገለጡላት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ ይህ ግሩም ድንቅ ምሥጢር ነው፡፡ አቤቱ ፈጣሪያችን ሆይ ሁሌም
ቢሆን ሞትህን እናስብ ዘንድ ፍቀድ ምክንያቱም ድንቅ የሆነውን የትንሣኤህን ምሥጢር አስቀድመህ ካናገርኸው ነቢያት ቃል ተነሥተን ወደፊት የሚሆነውን እያሰብን
የዚህችን ዓለም ኑሮ እንዘነጋት ዘንድ፡፡ ክብር ምስጋን ለአንተ ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
Kale Hiwoten Ya'semalen!
ReplyDeletekale hiwot yasemalen
ReplyDelete