Monday, March 12, 2012

ምጽዋት በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
03/07/2004 
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር መብራታቸውን ከዘይታቸው ጋር አስተባብረው ይዘው የተገኙት ደናግላን ወደ ሰርጉ እንዲታደሙ እንዳደረጋቸው ገልጦልናል፡፡ በዘይት የተመሰለው ተግባራዊ ምልልሳችን ሲሆን እርሱም የእግዚአብሔር ስም በእኛ ይበልጥ እንዲከብርና እንዲመሰገን ያደርገዋል፡፡ ይህም የጽድቅ ሕይወታችን ለሌሎች ብርሃን ለመሆን እንድንበቃ ያግዘናል፡፡ ስለዚህም ነው ጠቢቡ ሰሎሞን “የጻድቅ መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው” ማለቱ፡፡ (ምሳ.4፡18) መንገድ የተባለው ለክርስቶስ ፈቃድ መታዘዛችን ነው፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ በማለት ያስተምረናል፤
“በመቅረዛችን ውስጥ ዘይቱን በመጨመር መንፈሳዊውን መብራት ደምቆ እንዲበራ እናድርገው፡፡ መሥዋዕት አድርገን የምናቀርበውን መብራት ሰማያዊውን ሙሽራ ለመቀበል የሚያገለግል መሥዋዕት ነው፡፡ እንዲያም ስለሆነ ከመቅረዙ ውስጥ ተጨማሪ ዘይት ሊጨመርበትና እስከ ላይ ደርሶ ሊበራ ይገባዋል፡፡ እንዲህ ካልሆነ መቅረዝ በመያዛችን ብቻ ከእግዚአብሔር ዘንድ አንዳች ዋጋን የምናገኝ አይደለንም፡፡ እንዲህም ስለሆነ ጌታችን “ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትን አይደለም” ብሎ አስተማረን ፡፡ (ማቴ.12፡7፤ሆሴ.6፡6)