በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
24/05/2004
ልጆቹ ያደረገን፣ ፍጹም ከሆነው
ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሣ “በመስፈሪያው የተጨቆነና የተትረፈረፈ ጸጋውንና በረከቱን ያደለን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይክበር ይመስገንና በረከት የሚባለው ቃል በውስጡ ከላይ ከእርሱ ከፍቅር አምላክ ዘንድ የሚሰጠውን ደግ ቸርነት የሚያውጅ ቃል ነው፡፡ በረከት የሚለው ቃል አንድ ጊዜ
ከእግዚአብሔር በተሰጠ ጸጋ ላይ ጭማሪ ወይም ድርጎ ሆኖ የሚሰጠውን የእግዚአብሔር ስጦታን ያመላክታል፡፡ በረከትን ለሁለት ከፍለን
መመልከት እንችላለን፡፡ ምድራዊ በረከትና መንፈሳዊ በረከት በማለት፡፡
v ምድራዊ በረከት
ምድራዊ በረከት እግዚአብሔር በድካማችን ጨምሮ የሚሰጠን ስጦታው ሲሆን የእግዚአብሔር የፍቅሩ መገለጫ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው እንደ ድካሙ
ብቻ መጠን ቢሰጠው ኖሮ ለነገ የሚያተርፈው አንዳች ነገር ባልኖረው ነበር፡፡ ነገር ግን በድካማችን ካፈራነው ላይ እግዚአብሔር የራሱን
ቸርነት ያክልበታል፡፡ እንዲህ እንደሆነ እንረዳም ዘንድ ጌታችን አምስቱን እንጀራና ሦስቱን ዓሣት ባርኮ ለአምስት ሺህ ሰዎች መግቦ
አጥግቦ አሳይቶናል፡፡ ይህም በሰዎች ኅሊና ውስጥ ሁልጊዜ እንዲታሰብም የተረፈውን በመሶብ ሰብስበው እንዲያስቀምጡት ሐዋርያትን አዘዛቸው፡፡(ማቴ.፲፭፥፴፪-፴፱)
የእግዚአብሔር ሰው የሆነውን የያዕቆብን እርሻ የባረከ አምላክ እንዲሁ የኃጥኡንም እርሻ ባርኳል፡፡(ሉቃ.፲፪፥፲፭-፳፪) እኛም ይህን በማወቅ በእምነት የማይመስሉንን ከመናቅና ከማቃለል እንዲሁም ከመጸየፍ ተቆጥበን የእርሱን ፍቅር ገንዘባችን አድርገን ከጠፉበት እንመልሳቸው ዘንድ እንዲገባን ሊያሳስበን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "በሰማይ ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ ... እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናብን ያዘንባል"(ማቴ.5፡43-46) አለን፡፡