ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
27/04/2009
መጽሐፍ ቅዱስ ሥጋንም ነፍስንም በተናጠል ሰውነት ይላቸዋል፡፡ ግዙፉን አካል ሰውነት እንዲለው አንዲሁ ቅዱስ ጳውሎስ “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ”(ኤፌ.3፡16-17) ብሎ እንደጻፈልን ረቂቋንም ነፍስ ውስጣዊ ሰውነት ይላታል፡፡ ይህ የተዋሕዶን ምሥጢር ለማስረዳት ትልቅ ቁልፍ ቃል ነው፡፡ ምንም እንኳ መጽሐፍ ሥጋንና ነፍስን በተናጠል ሰውነት ይበላቸው እንጂ ሰውነታችን አንድ ነው፤ ሁለት አይደለም፡፡ ሰውነት ስንል ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የሥጋና የነፍስ አንድነት ስያሜ ነው፡፡ ሥጋና ነፍስ ፍጹም በሆነ ተዋሕዶ አንድ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን የየራሳቸው ግብር አላቸው ቢሆንም በተናጠል አይደለም፡፡
በክርስቶስም የምናየው ይህንን ነው፡፡ እርሱ “እንግዲህ የሰው ልጀ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?” በሚለው ቃሉ ለሰው ልጅነቱ ቅድምና ሰጥቶ መናገሩን እናስተውላለን፡፡ “በሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው”(ዕብ.2፡17) የሚለው ደግሞ ሰዋዊ ማንነቱ እንዳልተለወጠ ያስገነዝበናል፡፡ በዚህ ማነንቱ ሆኖ አምልኮ ለእርሱ ለእግዚአብሔር በግ ቀረበለት፡፡ ጌታ ተወለደልን ተባለ፤ ሕፃን ሳለ አምልኮን ከሰብአ ሰገል ተቀበለ፡፡ አንድያ የአግዚብሔር ልጅ፣ አምላክ፣ እግዚአብሔርም ተባለ፤ በደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ” ተብሎ”ደሙ" የእግዚአብሔር ደም ተባለ፡፡ በዚህም መለኮታዊ ልዕልናውን የሰው ልጅ ሲል እኛንም በመምሰሉ ራሱን የሰው ልጅ ብሎአል፡፡ ለሁለቱም ማንነቱ አንድ "የሰው ልጅ" የሚለውን ስያሜ ተጠቀመ፡፡ ይህም ከድንግል የተካፈለውን ሰውነት ከመለኮታዊ ልዕልናው መለኮታዊ ልዕልናውን ከሰውነቱ ነጣጥሎ እንዳላስተማረን በተረዳ ነገር ታወቀ፡፡ በዚህ ጥቅስና በሌሎችም ጥቅሶች ጌታችን የተዋሕዶውን ምሥጢር ገለጸልን፡፡