Monday, May 21, 2012

“መስቀል ለእኔ”



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
14/09/2004
መስቀል ስል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ያን መስቀል ማለቴ ነው፡፡ እንዲያም ሲሆን ደግሞ እንደመንፈሳዊ ትርጉሙ እንጂ  እንደ ሥጋዊያን አይደለም አረዳዴ፡፡ እነርሱ በመስቀሉ ክርስቶስን አይመለከቱትም፤ በክርስቶስ ደግሞ የመስቀሉን መንፈሳዊ ትርጉም አይረዱት ቁሳውያን ናቸው ፡፡ እግዚአብሔር የእውቀቱን ደጅ ይክፈትላቸው፡፡ ታመዋል ወይም እነዚህ ወገኖች ጣዖት አምላኪያን ሆነዋል፡፡ ሰዎችን እንዲህ እንዲስቱ  የሚያደርጋቸው ደግሞ ሰይጣን ነው፡፡ የእርሱ ፈቃድ በምንም ዓይነት መንገድ የክርስቶስ ስም እንዳይጠራ ማድረግ ነው፡፡ አቤቱ አምላኬ ስለምወዳቸው ስለእነዚህ በአመለካከታቸው  ገና ወተት ላይ ላሉት ማስተዋልን ስጣቸው፡፡ ፈቃድህን ተረድተው እንደተርብ ከመናደፍ እንዲመለሱ እርዳቸው፡፡ መስቀል ለእኔ መንግሥተ ሰማያት ማለት ነው ከጌታዬ ከአምላኬ ከአባቴ ከአፍቃሪዬ ከክርስቶስ ጋር የምኖርበት ቤቴ ነው፡፡
በመስቀሉ ለክርስቶስ ኢየሱስ አፍቃሪያን ሁለት ምግቦች ተሰጥተዋል፡፡ አንደኛው ፍቅር ነው፡፡ሁል ጊዜ ወደ መስቀሉ ስመለከት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ስለማፍቀሩ የተቀበለውን ጽኑ መከራ አስባለሁ፡፡እኛን ለማዳን ሲል የተቀበለውን መከራ ሳስብ ደግሞ ጥልቅ የሆነውን ፍቅሩን አስተውለዋለሁ፡፡ ስለእኛ መሞቱ ግድ ቢሆንም የተቀበለውን መከራ ሳስታውስ በከባድ ኃዘን ውስጥ እወድቃለሁ፡፡ ኃጢአቴም ትዝ እያለኝ የተዋለልኝን ውለታ ዘንግቼ እርሱን ጌታዬን በማሳዘኔ ቁጭት ሃዘን ይነግሥብኛል፡፡ በዚህም ምክንያት እኔ ከልጆቹ ልቆጠር የማይገባኝ ሲኦል ስለኃጢአቴ የምታንሰኝ እንደሆነች ሆና ትሰማኛለች፡፡ ኦ ፍቅርን እኮ ነው የበለደልኩት!!!