Monday, May 21, 2012

“መስቀል ለእኔ”



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
14/09/2004
መስቀል ስል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ያን መስቀል ማለቴ ነው፡፡ እንዲያም ሲሆን ደግሞ እንደመንፈሳዊ ትርጉሙ እንጂ  እንደ ሥጋዊያን አይደለም አረዳዴ፡፡ እነርሱ በመስቀሉ ክርስቶስን አይመለከቱትም፤ በክርስቶስ ደግሞ የመስቀሉን መንፈሳዊ ትርጉም አይረዱት ቁሳውያን ናቸው ፡፡ እግዚአብሔር የእውቀቱን ደጅ ይክፈትላቸው፡፡ ታመዋል ወይም እነዚህ ወገኖች ጣዖት አምላኪያን ሆነዋል፡፡ ሰዎችን እንዲህ እንዲስቱ  የሚያደርጋቸው ደግሞ ሰይጣን ነው፡፡ የእርሱ ፈቃድ በምንም ዓይነት መንገድ የክርስቶስ ስም እንዳይጠራ ማድረግ ነው፡፡ አቤቱ አምላኬ ስለምወዳቸው ስለእነዚህ በአመለካከታቸው  ገና ወተት ላይ ላሉት ማስተዋልን ስጣቸው፡፡ ፈቃድህን ተረድተው እንደተርብ ከመናደፍ እንዲመለሱ እርዳቸው፡፡ መስቀል ለእኔ መንግሥተ ሰማያት ማለት ነው ከጌታዬ ከአምላኬ ከአባቴ ከአፍቃሪዬ ከክርስቶስ ጋር የምኖርበት ቤቴ ነው፡፡
በመስቀሉ ለክርስቶስ ኢየሱስ አፍቃሪያን ሁለት ምግቦች ተሰጥተዋል፡፡ አንደኛው ፍቅር ነው፡፡ሁል ጊዜ ወደ መስቀሉ ስመለከት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ስለማፍቀሩ የተቀበለውን ጽኑ መከራ አስባለሁ፡፡እኛን ለማዳን ሲል የተቀበለውን መከራ ሳስብ ደግሞ ጥልቅ የሆነውን ፍቅሩን አስተውለዋለሁ፡፡ ስለእኛ መሞቱ ግድ ቢሆንም የተቀበለውን መከራ ሳስታውስ በከባድ ኃዘን ውስጥ እወድቃለሁ፡፡ ኃጢአቴም ትዝ እያለኝ የተዋለልኝን ውለታ ዘንግቼ እርሱን ጌታዬን በማሳዘኔ ቁጭት ሃዘን ይነግሥብኛል፡፡ በዚህም ምክንያት እኔ ከልጆቹ ልቆጠር የማይገባኝ ሲኦል ስለኃጢአቴ የምታንሰኝ እንደሆነች ሆና ትሰማኛለች፡፡ ኦ ፍቅርን እኮ ነው የበለደልኩት!!!


ቢሆንም በእርሱ ስቅለት ያገኘሁትን ጸጋ ሳስታውስ ወደ መጽናናት እመጣለሁ፡፡ በመስቀሉ ከእርሱ ጋር ሞቼ ከእርሱ ጋር ሞትን ድል እድርጌ ተነሥቻለሁ ፡፡ መስቀሉ ማዕድ ከሥጋው በልቻለሁ ከደሙም ጠጥቻለሁ ፡፡ በመስቀሉ  አዲስ ሕይወትን ገንዘቤ አድርጌአለሁ ፡፡ እንዲህ ንጹሕ አድርጎኝ ካበቃ በኋላ ንኳ ብበድለውና ስለኃጢአቴ ተጸጽቼ ንስሐ ብገባ በፍቅር አቅፎ ሊቀበለኝ ዝግ ነው ፡፡ በዚህጥልቅ የሆነውን ለእኛ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር አስታውሼ ከፍቅሩ እጠግባለሁ፡፡ ለራሴም ፍቅርን ዳግም ላለማሳዘን ቃል እገባለሁ፡፡ በዚህ ደስ ይለኛል፡፡  መስቀል ማለት ጥምቀት ማለት ነው ፡፡ በጥምቀት ከጌታችንና ከአፍቃሪያችን ከክርስቶስ ጋር በሞቱ ተባብረን በትንሣኤው ደግሞ ተካፋዮች እንሆናለን አሁንም በእምነት ከእርሱ ጋር ተነሥተናል(ቆላ.፪፥፲፪)፡፡
 ስለዚህም  እርሱ በአብ ቀኝ እንዳለ  ሕይወታችንም ከእርሱ ጋር በአብ ቀኝ ናት “ሞታችኋልና ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና ፥ ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ”(ቆላ.፫፥፩-፬)እንዲል፡፡ አሮጌው ሰዋችንም ከእርሱ ጋር ተሰቅሎአል ፤ በጥምቀትም አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለብሰነዋል(ኤፌ.፪፥፲፡)፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ እኔ ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለው እምነት የምኖረው ነው”አለ፡፡(ገላ.፪፥፳) በዚህም ፍጹም ደስታ ይሰማኛል፡፡ ይህ ሳውጠነጥን ስለዓለሙ ማሰብን አቋርጣለሁ፡፡ ፍቅሩን አስተውዬ እጠግባለሁ ፡፡ ስለዚህ ከመስቀል መውጣት አልፈልግም በዚህ በተወሰነ መንፈሳዊ የፍቅር ዓለም(መስቀል)ላይ በቦታ የማይወሰነውን እናገኘዋለን፤ ከእርሱም ጋር ፍጹም የሆነ ሕብረትም እንዲኖረን ተደርገናል፡፡ በጥምቀት ክርስቶስን ከመልበሳችን የተነሣ በመስቀሉ አንድ አካል ስንሆን፣ እያንዳንዳችን ደግሞ አንዱ ለአንዱ ሕዋስ ሆነናል፡፡
በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮችን ሁሉ ከመስቀሉ ካልወጣን በቀር አይጓደልብንም፡፡ በመስቀሉ ፍቅሩን ሥጋውንና ደሙን እንመገባለን፣ በመስቀሉ በጠቀለለን ክርስቶስ እቅፍ ውስጥም እንጠለላለን፤ ከእርሱ እጅ ማንም ሊነጥቀን አይችልም፡፡(ዮሐ.፲፥፳፰) በመስቀሉ እርሱን ክርስቶስን ለብሰነዋል(ገላ.፫፥፳፮-፳፯) ታዲያ ምን ጎደለብኝ፡፡ ሐዋርያውም “ ምግብና ልብስ ከኖረን እርሱ ይበቃናል” ብሎአል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ጋር ፈጽሞ የማይወዳደር ሰማያዊ ምግብና ልብስ እንዲሁም ሐዋርያው ያልጠቀሰው መጠለያም አግኝተናል እርሱም ክርስቶስ ነው፡፡
 በመስቀሉ በደስታ ወደ ተሰበሰቡ አእላፍት ቅዱሳን መላእክት፣ ወደ ቅዱሳን ነፍሳት፣ ደርሰናል፡፡ ከዚህ መስቀል ላይ ከተሠዋው መድኅናችን ጌታችን አምላካችን አፍቃሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጎን ከአቤል ደም ይልቅ ይቅርታን የሚያሰጥ እንጂ የሚካሰስ ያይደለ ደም  ስለብዙዎች የኃጢአት ስርየት ይፈሳል፡፡ ከዚህ የዓለምን ኃጢአት ሁሉ ከሚያስወግደው ደም የተቀበለ ሰው እርሱ በደሙ ተረጭቶአል፡፡ ወደ ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም፣ ወደ እግዚአብሔር ከተማ  ወደ ጽዮን ተራራ ወደበኩራት ማኅበር ደርሷል(ዕብ.፲፪፥፳፩-፳፬)፡፡ ይህ ነው የመስቀሉ መንፈሳዊ ትርጉም፡፡
 መስቀል ማለት ወንጌል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ወንጌል በመስቀሉ ላይ ስለተሰቀለው ጌታ የሚተርክ ነው፡፡ ይህንን ሐዋርያው “የመስቀሉ ቃል" ብሎታል፡፡(፩ቆሮ.፩፥፲፰) ከካህናት አባቶቼ እጅ የመስቀሉን ምሳሌ ስመለከት ወንጌልን አስታውሳለሁ፡፡ እነርሱም “እኛስ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” ሊሉ ይገባቸዋል፡፡ እኔም አአምን በቃለ ወንጌልከ ቅዱስ ብዬ ልሳለመው ይገባኛል”ይህ ነው መስቀል ለእኔ፡፡ ስለዚህም ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር "...ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልኩበት ከጌታዬ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ፡፡"እላለሁ እንላለን እኛ ኦርቶዶክሳዊያን፡፡(ገላ.6፡11)

1 comment:

  1. በመስቀሉ በደስታ ወደ ተሰበሰቡ አእላፍት ቅዱሳን መላእክት፣ ወደ ቅዱሳን ነፍሳት፣ ደርሰናል፡፡ ከዚህ መስቀል ላይ ከተሠዋው መድኅናችን ጌታችን አምላካችን አፍቃሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጎን ከአቤል ደም ይልቅ ይቅርታን የሚያሰጥ እንጂ የሚካሰስ ያይደለ ደም ስለብዙዎች የኃጢአት ስርየት ይፈሳል፡፡ ከዚህ የዓለምን ኃጢአት ሁሉ ከሚያስወግደው ደም የተቀበለ ሰው እርሱ በደሙ ተረጭቶአል፡፡ ወደ ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም፣ ወደ እግዚአብሔር ከተማ ወደ ጽዮን ተራራ ወደበኩራት ማኅበር ደርሷል(ዕብ.፲፪፥፳፩-፳፬)፡፡ ይህ ነው የመስቀሉ መንፈሳዊ ትርጉም፡፡

    ReplyDelete