በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
30/06/2004
የሰው ልጅ ከሦስት አካላት ጋር
ኅብረት ያለው ፍጥረት ነው፡፡ አንደኛው ከምድር ፍጥረታት ጋር ሲሆን እርሱ ገዢያቸው ነውና በገዢና በተገዢ መካከል እንዳለ ዓይነት ኅበረት ከእነርሱ ጋር ይኖራል፡፡ ሌላኛው ከመላእክት ጋር ነው፤ መንፈሳዊት ረቂቅ አካል ስላለችው ከመላእክት ጋርም ኅበረት አለው፡፡ ሦስተኛውና ዋነኛው
የሁለቱ ውሕደት ውጤት የሆነው የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ አለውና ከእግዚአብሔር አምላኩ ጋር ኅብረት አለው፡፡
ሰው ከእነዚህ ከሦስት አካላት መካከል ከአንዱ ጋር ኅብረቱ ከተቋረጠ ሕይወቱ
ጣዕም ታጣለች፡፡ እነዚህ ኅብረቶች የሰው ልጆችን ሙሉ የሚያደረጓቸው ኅብረቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ በሰውነታችን ውስጥ አሉ፡፡ ፍጥረታዊውን ዓለም የምትወክል
ከምድር አፈር የተበጀት ሰውነት አለች፡፡ ሰማያውያን መላእክትን የምትወከል ረቂቅ ነፍስ አለችን፡፡ረቂቃንንና ግዙፋንን በአንድነት የሚገዛ
ስለመሆኑ ምስክር የምትሆን የእግዚአብሔር የገዢነቱ ምልክት የምትሆን "እኔ" የምንላት ማንነት አለችን፡፡ በሥጋ ተፈጥሮአችን ምድራውያን ፍጥረታትን ብንመስልም እነርሱን ሙሉ ለሙሉ መስለን
መኖር አንችልም፡፡ በነፍስ ተፈጥሮአችን መላእክትን ብንመስለም ሙሉ ለሙሉ በእነርሱ ሥርዐት ልንኖር አይቻለንም፡፡ እኛ ከሁለቱ
በተውጣጣ ሥርዐት እንኖራለን፡፡ ስለዚህም ሰው አኗኗሩን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ ካሻ እነዚህን ሁለቱን ፍጥረታት በተፈጥሮው
በኩል ማወቅና መረዳት ይገባዋል፡፡