በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
30/06/2004
የሰው ልጅ ከሦስት አካላት ጋር
ኅብረት ያለው ፍጥረት ነው፡፡ አንደኛው ከምድር ፍጥረታት ጋር ሲሆን እርሱ ገዢያቸው ነውና በገዢና በተገዢ መካከል እንዳለ ዓይነት ኅበረት ከእነርሱ ጋር ይኖራል፡፡ ሌላኛው ከመላእክት ጋር ነው፤ መንፈሳዊት ረቂቅ አካል ስላለችው ከመላእክት ጋርም ኅበረት አለው፡፡ ሦስተኛውና ዋነኛው
የሁለቱ ውሕደት ውጤት የሆነው የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ አለውና ከእግዚአብሔር አምላኩ ጋር ኅብረት አለው፡፡
ሰው ከእነዚህ ከሦስት አካላት መካከል ከአንዱ ጋር ኅብረቱ ከተቋረጠ ሕይወቱ
ጣዕም ታጣለች፡፡ እነዚህ ኅብረቶች የሰው ልጆችን ሙሉ የሚያደረጓቸው ኅብረቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ በሰውነታችን ውስጥ አሉ፡፡ ፍጥረታዊውን ዓለም የምትወክል
ከምድር አፈር የተበጀት ሰውነት አለች፡፡ ሰማያውያን መላእክትን የምትወከል ረቂቅ ነፍስ አለችን፡፡ረቂቃንንና ግዙፋንን በአንድነት የሚገዛ
ስለመሆኑ ምስክር የምትሆን የእግዚአብሔር የገዢነቱ ምልክት የምትሆን "እኔ" የምንላት ማንነት አለችን፡፡ በሥጋ ተፈጥሮአችን ምድራውያን ፍጥረታትን ብንመስልም እነርሱን ሙሉ ለሙሉ መስለን
መኖር አንችልም፡፡ በነፍስ ተፈጥሮአችን መላእክትን ብንመስለም ሙሉ ለሙሉ በእነርሱ ሥርዐት ልንኖር አይቻለንም፡፡ እኛ ከሁለቱ
በተውጣጣ ሥርዐት እንኖራለን፡፡ ስለዚህም ሰው አኗኗሩን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ ካሻ እነዚህን ሁለቱን ፍጥረታት በተፈጥሮው
በኩል ማወቅና መረዳት ይገባዋል፡፡
ሰው ረቂቁን እግዚአብሔርን ከሚታዩት
ፍጥረታት መማር ይጀምራል፡፡ ሥነፍጥረት ስለእግዚአብሔር ሕልውና አዋጅ ነጋሪዎች ናቸው፡፡ እንዲህ እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች
“የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኀይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና”(ሮሜ.2፡20-21)ብሎ
በግልጽ አስፍሮልን እናገኛለን፡፡ በሚታዩት ሥነፍጥረት
የእግዚአብሔርን
መጋቢነት ጥበብና ፍቅር እንዲሁም ሥርዐት ወዳድነት እንማራለን፡፡ ይህ ግን ብቻውን በቂ አይደለም ነገር ግን በቂ ስላልሆነ የምንተወውም ትምህርት አይደለም፡፡ እነዚህ እግዚአብሔርን ለማወቅ ልክ እንደ ፊደል ገበታዎች ናቸው፡፡ አንድ ሰው የፊደል ሠራዊቶችን ሳይለይ
ማንበብ እንዳይችል እንዲሁ በሥነፍጥረት የእግዚአብሔር ሕልውናና ፈቃድ ሳይረዳ ሰውንም ቢሆን እግዚአብሔርን ማወቅ አይችልም፤ ይህ ተፈጥሮአዊ ሕግ ይባላል፡፡
የራስን የተፈጥሮ ጠባይ መረዳት፤ አካባቢን ማወቅ የሕይወት ሥርዐታቸውን መገንዘብ የመጀመሪያ
ቀዳሚው ሕግ ነው፡፡ እነዚህ ፍጥረታት እኛንም ጨምሮ በራሳቸው የእግዚአብሔር ማስተዋል ፈጽሞ የማይመረመር፣ ኃያል፣ የፈቃዱን የሚፈጽም መሆኑን
በፀጥታ ሆነው ይሰብኩናል፡፡ ነገር ግን እነዚህ የእርሱን ማንነት እኛ እንደሚጠበቅብን ያህል ሊያስረዱን አይችሉም፡፡ ስለዚህም
ወደ ሁለተኛው እርከን ከፍ እንላለን፡፡ ረቂቁን ዓለም ወደማስተዋል እንመጣለን፡፡ ያም ማለት ወደ ነፍሳችን ተፈጥሮ እንመጣለን፡፡
በመስታወት ወይም በሰው ራሳችንን እንድንመለከት እንዲሁ የነፍሳችንን ውበትና ተፈጥሮ መረዳት የምንችለው መላእክትን ያወቅናቸው እንደሆነ
ነው፡፡ እነርሱ ነፍሳችንን የምናይባቸው መስታወቶቻችን ናቸው፡፡
የዛሬውን አያድርገውና በገነት አዳምና ሔዋን ይህችን መልካቸውን መላእክትን
በመመልከት ልክ እኛ ሥጋችንን የምናቃትን ያህል ነፍሳቸውን ያውቋት ነበር፡፡ እኛ ግን እነርሱን ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ ወይም በታላቅ የቅድስና ሕይወት ውስጥ መገኘት ይኖርብናል፡፡
ነገር ግን እኛ አንያቸው እንጂ እነርሱስ በዙሪያችን ናቸው ፡፡ እነርሱ ያዩናል እኛ ግን የነፍሳችን ዐይኖች ስለታወሩ ልንመለከታቸው አልቻልንም፡፡ ይህ
ብቻ አይደለም እኛን ወደ ክፋት የሚመሩንን ሰይጣንንና ሠራዊቱን መመልከት ባለመቻላችን ሁልጊዜ በእነርሱ ስንሰነካከል እንኖራለን፡፡
ይህን እንደ ምሳሌ ላስቀምጥላችሁ፡፡ አዳም የተለየው ከዚህች ምድር ፍጥረታት
ነው ብለን እናስብ፡፡ ዘመኑም ከመላእክት ኅበረት ከገነት የወጣንበትን ዘመንን ያህላል እንበል፡፡ አኗኗራችን በእነርሱ የአኗኗር
ሥርዐት ነውም ብለን እናስብ፤ አንበላም፣ አንጠጣም ወዘተ… ይህን በዐይነ ሕሊናችን እንሳለው፡፡ ምን ይሰማችኋል? እንዲህ ዓይነት አኗኗር ቢኖረን
ኖሮ በእውኑ ነፍሳችንን ልክ እንደ ሥጋ ተፈጥሮአችን ምን እንደምትመስል ልናውቃት አንችልም ነበርን? የምድር ፍጥረታትን እንደምናውቃቸው መጠን መላእክትን አናውቃቸውም ነበርን? ነገር ግን ከእነርሱ ኅብረት ከተለየን ቆይተናልና የነፍሳችንን መልክና ገጽታ ማወቅና እነርሱንም መረዳት ተሳነን፡፡
ነገር ግን በሐዲስ ኪዳን ያፈቀረን አምላክ ይክበር ይመስገንና የክርስቶስን
አምላክነት ካመንንና ለፈቃዱ ከታዘዝን ቅዱሳን መላእክትን ስለምናያቸው በዛውም የነፍሳችንን መልክና ውበት ማየት እንችላለን፡፡
ይህን እርግጠኞች እንድንሆንም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለናትናኤል “እውነት እውነት እላችኋለሁ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም
መላእክት ወደ ሰው ልጅ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” ብሎ አስተማረን፡፡(ዮሐ.1፡52) እግዚአብሔርን መምሰላችንን ግን በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በቀላሉ
መረዳት እንችላለን፡፡ እርሱ የመናፍስትና የግዙፋኑ ፍጥረታት ገዢ እንደሆነ እንዲሁ እኛም ቅዱሳን መላእክት ላይ የምንሠለጥን ባንሆንም
የእርሱ መልክ ስላለን ሲያገለግሉን፤ ግዙፋን ፍጥረታትም ለእኛ ሲገዙልን ይታያሉ፡፡
በነገራችን ላይ የደማስቆው ቅዱስ ዮሐንስ እርሱም ከቅዱሳን አባቶች አገኝቶ ሲያስተምር በገነት የተተከለችው ዕፀ በለስ ዛፍ ሳትሆን በተፈጥሮአችን የተሠራችው "ራስን ማስተዋል" ናት ይለናል፡፡ ሰው እግዚአብሔርን በማወቅ አእምሮው ሳይደረጅ ፍቅሩን በጥልቀት ሳይረዳ ጣዕሙንም ቀምሶ ሳያጣጥመው ራሱን ወደ ማስተዋል
ቢመልስ ያለጥርጥር በትዕቢት ተይዞ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ የሚከሰትበት የእድሜ ክልል ደግሞ ወጣትነት ነው፡፡ ብዙዎቻችን
ኃጢአትን የምንተዋወቃት በዚህ እድሜአችን ነው፡፡ በዚህ እድሜአችን ነገር ዓለማችንን ትተን ራሳችንን ለማሽሞንሞንና ለማስጌጥ እንደክማለን፣ ከሰዎች በተለይ ከፆታ ተቃራኒዎቻችን ሙገሳን፣ መወደድን፣ መፈለግን እንሻለን፡፡
ወደ እዚህ እድሜ ክልል ሳንደርስ
ራሳችንን ወደ መመልከት አንመጣም፤ በተለይ በሕፃንነታችን ወራት ነውራችንን እንኳ የሚሸፍኑልን እናቶቻችንና አባቶቻችን ናቸው፡፡ ነገር ግን በወጣትነታችን እድሜ ተፈጥሮ
ራሱዋ ሰውነታችንን እንድናስተውለው ታነሣሣናለች፡፡ ውበትንና ደምግባትን እንዲሁም የሚያምር ቅርጽና መልክን በዚህ እድሜአችን ገንዘባችን
እናደረጋለን፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ ነውና አንዳች ጉድለት የለበትም፡፡ ነገር ግን ወደዚህ እድሜ ከመድረሳችን በፊት እግዚአብሔርንና
ፈቃዱን ማወቅ እንዲሁም ፍቅሩን ማስቀደም ከእኛ ዘንድ ካለ በዚህ እድሜ የሚገጥመን “ራስን ማስተዋል”
አያሰነካክለንም፤ እንዳውም አምላካችንን ልክ እንደ ነቢዩ ዳዊት “አቤቱ አንተ ኩላሊቴን ፈጥረሃልና በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛልና ግሩምና ድንቅ
ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ” ብለን እናመሰግነዋለን፡፡(መዝ.138፡13-14)
እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ አስተምህሮ አዳምና ሔዋን ራሳቸውን ማስተዋል
ካለባቸው የእውቀት ከፍታ ሳይደርሱና ከእግዚአብሔር አምላካቸው ጋር ሳይላመዱ በነበሩበት ጊዜ ነበር ሰይጣን ወደ እነርሱ በመቅረብ
ራሳቸውን ወደ ማስተዋል መልሶ በራሳቸው ተፈጥሮ ተሰነካክለው እንዲወድቁ ያደረጋቸው፡፡ አዳምና ሔዋን
ራሳቸውን ወደማስተዋል በምጣታቸው ዕራቁታቸውን መሆናቸውን ተረዱ፤ ስለዚህም የበለስ ቀጠል ሰፍተው ለራሳቸው አገለደሙ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ
አዳምን በገነት “ወዴት ነህ? ብሎ በተጣራም ጊዜ “በገነት ድምፅህን ሰማሁ ዕራቁቴንም ስለሆንሁ ፈራሁ ተሸሸግሁም አለው” ነገር ግን አስቀድሞም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ “አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ አይተፋፈሩም ነበር” ይለናልና በእርግጥም ዕራቁታቸውን ነበሩ፡፡ ይህንን ዕራቁትነት ቅዱስ ኤፍሬም በዕንቁ ይመስለዋል፡፡ እነርሱ ምንም እንኳ ከልብስ የተራቆቱ ቢሆኑም ልክ እንደ ዕንቁ ከውስጣቸው ከሚመነጨው ብርሃን የተነሳ ገላቸው አይታይም ነበር፡፡ ነገር ግን አዳምና ሔዋን አስቀድሞም ዕራቁታቸውን ካልሆኑ በቀር እንዴት ዕራቁታቸውን መሆናቸውን አወቁ? እንዲህም ስለነበር በገነት እግዚአብሔር አምላክ “ዕራቁትህን እንደ ሆንህ ማን ነገረህ?ብሎ አዳምን ጠየቀው፡፡
ለአዳምና ለሔዋን ራሳቸውን የሚያስተውሉበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ እንዳልነበሩ መረዳት የምንችለው "ራስን የማስተዋል" ሃሳብ ከእነርሱ ሳይሆን ከሰይጣን በመመንጨቱ ነው፡፡ እንደ ቅዱሱ ገለጻ ከሆነ ዕፀ በለሱዋ በገነት አልቀረችም፤ እነሆ አሁንም በተፈጥሮአችን ውስጥ ተተክላ አለች፡፡ እግዚአብሔርን አውቀን፣ ጣዕሙን ቀምሰን፣ ፍቅሩን ተረድተን፣ ራሳችንን የተመለከትንና ያስተዋልን ከሆንን ይበልጥ ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅር እንጣበቃለን እንጂ ራሳችንን በማስተዋላችን አንሰነካከልም፡፡ ነገር ግን እርሱን ባለማወቅ ሆነን ራሳችንን ወደ ማስተዋል ከመጣን አይጣል ጥፋታችን!!! ብዙዎቻችን በዚህ ተሰነካከልን፣ በኃጢአት ተጨማለቅን ስለዚህም እግዚአብሔር አምላካችንን የምናይበት ዐይናችን ታወረ፡፡ ነገር ግን የሚወደን አምላክ አሁንም ከጥፋታችን እንመለስ ዘንድ የንስሐ እድሜንና ራስን መፈለግን ሰጥቶናል፡፡ አስቀድመን ጽድቁንና መንግሥቱን እንሻ እርሱ በተገቢው ጊዜና ሰዓት ራሳችንን እንድናስተውልና ተፈጥሮአችንን እንደርሱ ፈቃድ እንድንመራው ይረዳናል፡፡ ስለዚህም የራሳችን በጎ የሆነ ተፈጥሮ እርሱን ባለማወቃችን ምክንያት ጠልፎ እንዳይጥለን እግዚአብሔር አምላክ እርሱን ማወቅንና በፍቅሩ መኖርን ይስጠን፣ ያብዛልንም ለዘለዓለሙ አሜን!!!
ለአዳምና ለሔዋን ራሳቸውን የሚያስተውሉበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ እንዳልነበሩ መረዳት የምንችለው "ራስን የማስተዋል" ሃሳብ ከእነርሱ ሳይሆን ከሰይጣን በመመንጨቱ ነው፡፡ እንደ ቅዱሱ ገለጻ ከሆነ ዕፀ በለሱዋ በገነት አልቀረችም፤ እነሆ አሁንም በተፈጥሮአችን ውስጥ ተተክላ አለች፡፡ እግዚአብሔርን አውቀን፣ ጣዕሙን ቀምሰን፣ ፍቅሩን ተረድተን፣ ራሳችንን የተመለከትንና ያስተዋልን ከሆንን ይበልጥ ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅር እንጣበቃለን እንጂ ራሳችንን በማስተዋላችን አንሰነካከልም፡፡ ነገር ግን እርሱን ባለማወቅ ሆነን ራሳችንን ወደ ማስተዋል ከመጣን አይጣል ጥፋታችን!!! ብዙዎቻችን በዚህ ተሰነካከልን፣ በኃጢአት ተጨማለቅን ስለዚህም እግዚአብሔር አምላካችንን የምናይበት ዐይናችን ታወረ፡፡ ነገር ግን የሚወደን አምላክ አሁንም ከጥፋታችን እንመለስ ዘንድ የንስሐ እድሜንና ራስን መፈለግን ሰጥቶናል፡፡ አስቀድመን ጽድቁንና መንግሥቱን እንሻ እርሱ በተገቢው ጊዜና ሰዓት ራሳችንን እንድናስተውልና ተፈጥሮአችንን እንደርሱ ፈቃድ እንድንመራው ይረዳናል፡፡ ስለዚህም የራሳችን በጎ የሆነ ተፈጥሮ እርሱን ባለማወቃችን ምክንያት ጠልፎ እንዳይጥለን እግዚአብሔር አምላክ እርሱን ማወቅንና በፍቅሩ መኖርን ይስጠን፣ ያብዛልንም ለዘለዓለሙ አሜን!!!
ዕራቁታቸውን ነበሩ አይተፋፈሩም ነበር” ይለናልና በእርግጥም ዕራቁታቸውን ነበሩ፡፡ ይህንን ዕራቁትነት ቅዱስ ኤፍሬም በዕንቁ ይመስለዋል፡፡ እነርሱ ምንም እንኳ ከልብስ የተራቆቱ ቢሆኑም ልክ እንደ ዕንቁ ከውስጣቸው ከሚመነጨው ብርሃን የተነሳ ገላቸው አይታይም ነበር፡፡ ነገር ግን አዳምና ሔዋን አስቀድሞም ዕራቁታቸውን ካልሆኑ በቀር እንዴት ዕራቁታቸውን መሆናቸውን አወቁ? እንዲህም ስለነበር
ReplyDeleteቃለ ህይወት ያሰማልን!!
ReplyDelete