Friday, February 24, 2012

ሠዓሊት በተፈጥሮ


ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
16/06/2004

እግዚአብሔር አምላክ ሴትን ልጅ ጥበብን የምትወድ ሠዓሊት አድርጎ ፈጠራት፡፡ ስለዚህም ውስጣዊውንና ውጫዊውን የሰውነት ክፍሎቹዋን እንደ ሸራ በመጠቀም ልታስተላለፍ የምትፈልገውን መልእክት በሰውነቱዋ ሸራ ላይ ትሥልልናለች፡፡ እኛም ወንዶች ደግሞ አድናቂዎቿና ተማሪዎቿ ነን፡፡ ባለን እውቀት ላይ ተጨማሪ እውቀቶችን ከእርሱዋ እንጨምራለን፡፡ እንዲህም ስለሆነ እነርሱ ሁል ጊዜ በሕሊናቸው የሚመላለሰውን በጎም ይሁን ክፉ አሳብ በሰውነታቸው ሸራ ላይ ለመሣል ሲተጉ እኛ ወንዶች ደግሞ ሥዕላቸውን አይተን ለማድነቅና ለመማር እንተጋለን፡፡ እነርሱ ልክ እንደ ሠዓሊ በዝምታ መልእክታቸውን በሰውነታቸው ሸራ ላይ ሲያስተላለፉ፤ እኛ ደግሞ በዝምታ የጥበብ ጥማችንን ስናረካና ከመልእክቶቻቸው ስንማር እንገኛለን፡፡
ይህን ግን ምናልባትም ዘመኑ የተረዳው አይመስለኝም፡፡ ሴትን ልጅ አታጊጪ ብሎ መከልከል አንድ ሠዓሊን አትሣል ብሎ እንደ መከልከል ይቆጠራል፡፡ ሠዓሊን አትሣል ብለን ብሩሹንና ሸራውን ልንቀማው እንችላለን፡፡ ሴትን ልጅ ግን አትሣዪ ብሎ በምን ማቆም እንዴት መከልከል ይቻላል? እርሱዋ ሥዕሉዋን መሣል የምታቆመው ይህችን ዓለም በሞት የተሰናበተቻት እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ለእርሱዋ ብሩሹዋ ማስተዋሉዋ ነው፤ ቀለሞቹዋም በነፍሱዋ ውስጥ ናቸው ሸራዎቹዋም ነፍስና ሥጋዋ ናቸው፡፡ በማስተዋል ብሩሽ፣ በነፍሱዋ ውስጥ ባሉ ቀለማት ነፍሱዋንና ሥጋዋን በውበት ታስጌጣቸዋለች፡፡