Thursday, September 13, 2012

ከራኬብ ምን እንማራለን? እስቲ እንወያይ



በዲ/ን ሽመልስ መርጊ
03/01/2005
ወገኖቼ እስቲ ዛሬ ይክበር ይመስገንና የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅም ቅም አያት ስለሆነችው ስለራኬብ ትንሽ እንወያይ፡፡ ራኬብ ቤቱዋን በኢያሪኮ ቅጥር ላይ ሠርታ በሴተኛ አዳሪነት ብዙዎችን ታወጣና ታገባ የነበረች በዚህም ቤተሰቡዋን የምትመራ ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ ግብጻውያንን በበረታ ክንዱ እንዳጠፋቸው በተረዳች ጊዜ የእስራኤላውያን አምላክ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ የተገነዘበች ሴት ነበረች፡፡ ይህች ሴት ኢያሱ ኢያሪኮን ይሰልሉ ዘንድ የላካቸውን ሁለት ሰላዮችን በቤቱዋ የተቀበለችና እነርሱን ከሚያሳደዱ ወታደሮች በመሸሸግ ያዳነቻቸው ሴት ነበረች፡፡ እንዲህም ማድረጉዋ በእምነት የእስራኤል አምላክ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ስለተረዳች እርሱዋንና ቤተሰቡዋን ለማትረፍ ስትል የፈጸመችው ነበር፡፡ ኢያሪኮ በእስራኤላውያን ከጠፋች በኋላ ግን ሰልሞን ሚስቱ አድርጎ አገባት፡፡ ከእርሱዋም ቦኤዝን ወለደ ቦኤዝም ከሩት ኢዮቤድን ወለደ ኢዮቤድም እሴይን ወለደ እሴም ንጉሥ ዳዊትን ወለደ፡፡ ከዳዊት ወገን ከሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያምም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶ አዳነን፡፡

መጽሐፍ ቅዱስና ኦርቶዶክሳዊነት



በዲ/ን ሽመልስ መርጊ
03/01/2005
ለአንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ማለት የፊደል ገበታ ማለት ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ሀሁ ያልቆጠረ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ በተናገረው ጊዜ ማን እንደተናገረው ለይቶ ማወቅ ይቸገራል፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ዮሐንስ ጨርሶ ላነበበ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን መልእክታት አንዱን ከአንዱ ጋር እያዛመደ መልእክት የሚሰጡ ቃላትን በመመሥረት የእርሱ ፈቃድ ምን እንደሆነ እንዲረዳው ያደርገዋል፡፡ ይህን ከተረዳ በኋላ ግን መንፈስ ቅዱስ ድምጹን ያሰማዋል፤ እርሱም ይሰማዋል፡፡ በእርሱም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ለመመላለስ የበቃ ይሆናል፡፡ ለእንዲህ ዓይነት ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ሌሎች ድጋፍ ሰጪ መርጃ መሳሪያዎች አያስፈልጉትም፡፡ ምክንያቱም እውቀትን በቀጥታ ከእውቀት ባለቤት መንፈስ ቅዱስ እየቀዳ ነውና፡፡