በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
24/06/2004
ዛሬ ባነሣሁት ጭብጥ ላይ:- ደግሞ ምን አመጣህ? ትሉኝ ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ ፍጥጥ ያለ እውነትና እውቀት ነው፡፡ ይህቺ እውነት እናቶቻችን፡- "ድሮ አግኝተናት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ይህች ዓለም የአውሬዎች መፈንጫ ባልሆነች ነበር" ብለው የሚቆጩባት እውነት ናት፡፡ ይህቺ እውቀትና እውነት ፡- ዓለምን ሴቶች ይገዙአትና ይመሩዋት ዘንድ ተፈጠረች የምትል ናት፡፡ መቼም ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ብላችሁ በመገረም ትጠይቁኝ
ይሆናል፡፡ እውነቱና ሐቁ ግን ይህ ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሴት ልጅ ገነትን እንደራሱዋ ሃሳብና ጥቅም ትመራትና
ትጠቀምባት ዘንድ በዚህም እርፍ ብላ ትኖርባት ዘንድ አዳምን ጨምሮ ሁሉን አደላድሎ ከፈጠረ በኋላ የፍጥረት ሁሉ ዘውድ አድርጎ ከአዳም
አስገኛት፡፡ አዳም አስቀድሞ በሥጋ መገለጡ ለእርሱዋ በእግዚአብሔር ፈንታ ሆኖ ገነትን እንዴት መምራትና ማስተዳደር እንደምትችል
ያስተምራት ዘንድ ነበር፡፡ በእርግጥም አዳም ይህን ፈጽሞላታል፡፡ ስለዚህም ነው ሰይጣን እርሱዋን በተንኮል “በእውኑ እግዚአብሔር
ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? ብሎ በጠየቃት ጊዜ “በገነት ካለው ዛፍ ፍሬ እንበላለን ነገር ግን በገነት መካከል ካለው
ከዛፉ ፍሬ እግዚአብሔር አለ፡-እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም”ብላ መመለሱዋ፡፡(ዘፍ.3፡2-3)