Sunday, December 30, 2012

“ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ”



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
22/04/2005
ከዚህ በፊት በማኅበረ ቅዱሳን ድኅረ ገጽ የተለቀቀ ጽሑፌ ነው፡፡
በዛሬው ቀን ዓለም ለመዳን የቅድስት ድንግል ማርያምን ይሁንታን የፈለገበት ቀን ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከምንም በላይ የሰውን ነጻ ፈቃድ ስለሚያከብር መልአኩን ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ሲልከው ፈቃዱዋን ይጠይቃት ዘንድ ነበር፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት መሰላችሁ “እነሆ በደጅህ ቆሜ አንኳኳለሁ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል”(ራእ.3፡20) እንዳለው ዓይነት ነው፡፡ ነገር ግን በይዘቱ የቅድስት እናታችን  ይሁንታ በጣም የተለየ ነው፡፡ ስለዚህም የዓለም መዳን በእርሱዋ ይሁንታ ላይ ነውና እግዚአብሔር በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በኩል የቅድስት ድንግል ማርያምን ፈቃድ ጠየቀ፡፡ ለእርሱዋም በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አንደበት እግዚአብሔር ቃል ለሰው ልጆች መዳን ከእርሱዋ ተፀንሶ ለመወለድ ፈቃዱ እንደሆነ፣ እርሱዋንም የዘለዓለም እናቱና የሰው ልጆችን ፍጹም የመውደዱ ምልክት ሊያደርጋት እንደወደደ አበሰራት፡፡ ቅድስት እናታችንም ፍጹም ትወደውና ታመልከው የነበረው እግዚአብሔር ከእርሱዋ ተወልዶ ዓለምን ለማዳን መፍቀዱን ስትሰማ በፍጹም ደስታ ተሞልታ ግሩም በሆነ ትሕትና “ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ” “እንደቃልህ ይደረግልኝ” በማለት ዓለምን እፎይ አሰኘቻት፡፡ እስከዛች ጊዜ ድረስ ዓለም በጭንቀት ተውጣ የእርሱዋን መልስ በጉጉት ትጠባበቅ ነበር፡፡