Tuesday, January 24, 2017

ፊደል ይገድላል መንፈስ ግን ያደናል



ዲ/ሽመልስ መርጊያ
16/05/2009

ጸሐፍት ፈሪሳውያን መጻሕፍትን በማወቅ የዘለዓለም ሕይወት የሚገኝ ይመስላቸው ነበረ፡፡ ነገር ግን ሕይወትን የሚሰጠው ወይም ሰውን ሕያው አድርጎ ሕያው የሆነውን ቃሉን እንዲረዳ የሚረዳው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ጸሐፊው መንፈስ ቅዱስ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ መረዳት የሚቻለው በመንፈስ እንጂ ስላነበቡት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ያነበበ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን አውቆአል ማለት  አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ከአእምሮ በላይ የሆኑ፤ ነገሮች ሳይፈጸሙ አስቀድሞ የሚያውቅ እርሱ እግዚአብሔር በመንፈሱ ያጻፈው ነውና፡፡ ስለዚህ ሊረዱዋቸው የሚቻለው በመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ነው፡፡ ስለዚህ መጻሕፍትን ለማስረዳት የተረዳነውን ለማብራራት የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ብቻኛ መንገድ ነው፡፡ ፍጥረታዊ በሆነ አእምሮ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት መሞከር እንደ ጸሐፍት ፈሪሳውያን መሆን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ይቀድማል ቅዱሳት መጻሕፍት ይከተላሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ይረዳል፡፡ 
ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ በእርሱ አሳሳቢነት እንደ አበው ቅዱሳን(ከአዳም -ሙሴ) ወይም እንደ ሐዋርያቱ በጽድቅ ጎዳና ሊራመድ ይችላል ነገር ግን መንፈሱ ያላደረበት አይሁዳዊ ከሆነ ግን የግድ መጽሐፍ በሚለው ብቻ ሊራመድ ይገደዳል፡፡ ቢሆንም ግን ያለመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ስለሆነ ማንበቡ ብቻውን ወደ መዳን አያደርሰውም፡፡ ቃል ይገድላል መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል እንዲል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ግን ቅዱሳት መጻሕፍትን ባነበበ ቁጥር ሁሉ በቀላሉ በመንፈስ ቅዱሰ ገላጭነት ይረዳቸዋል፡:
 በእርግጥ በመጻሕፍት ብቻ ሕይወት የሚገኝ ለሚመስላቸው ወገኖች የመንፈስ ቅዱስን ድጋፍ ስለማያውቁ መንፈስ ቅዱስን ሊሰሙት ሊረዱትንም አይችሉም፡፡ ስለዚህ ክርስቶስን ሊያውቁት ሊረዱት አልቻሉም፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎችን የሚያሰናክለው ያለ መንፈሰ ቅዱስ ድጋፍ በአእምሮ ጠባያቸው ብቻ ተደግፈው መጻሕፍትን እንረዳ ባሉ ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ስለ ክርሰቶስ ያላቸው ግንዛቤ እጅግ የተዘበራረቀ ይሆናል፡፡ ወይም በቀጥታ ቃሉን ይዘው ሰማያዊ የሆነውን እንደ አእምሮ ጠባያቸው በመረዳት ምድራዊ ያደርጉታል፡፡  መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ግን በመንፈስ የተጻፈውን ይረዳል፤ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሁሉን ይተነትናል ሲያብራራም ለሕሊናችን፣ ለተፈጥሮአችን የሚስማማ በመሀኑ ነፍሳችን ትፈካለች ፡፡ ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ ይቀድማል፡፡ ኦርቶዶክስ እንዲህ ናት ይህም ማለት ከጥንት የነበረችው እስካሁንም ያለችው ለዘለዓለም ሕያዊት ሆና የምትኖረዋ ክርስትና ማለቴ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment