Tuesday, January 24, 2017

ጸሎት በእንተ ትዳር

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
16/05/2009

ጌታ ሆይ ከእናቴ ሆድ ግሩምና ድንቅ አድርገህ ፈጠርኸኝ፡፡ ይህ ተፈጥሮዬም ግሩምና ድንቅ መባሉ በውስጥም በውጪም አንተን እንዲመስል ሆኖ መፈጠሩ ነው፡፡ ወንድና ሴት አድርገህ እንደፈጠርኽን ተናግረህ ካበቃ በኋላ አስቀድመህ የፈጠርኸው  ግን አዳምን ነበር፡፡ በእርሱ ውስጥ ሔዋን እንዳለች ግን አልተረዳንም ፡፡ ጌታ ሆይ ሥራህ ረቂቅ ነው፡፡ አንተ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር በማለት እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና በምሳሌው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠረው” ብለህ አስቀድመህ ሙሴን አጻፍኸው እንዲያም ሆኖ ግን “ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም” ብለህ በውስጡ የነበረችውን ሴትን በእርሱ ላይ ከባድ እንቅልፍን በማምጣት ፈጥረህ አሳየኸው፡፡ እርሱም ይህቺ ሴት ከአጥንቴ አጥንት ከሥጋዬም ሥጋ ናት ስለዚህ ሴት ትባል አለ፡፡ አንተም ሰው እናትና አባቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፡፡ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” አልህ፡፡ ስለዚህ በልዩነት ውስጥ ወደ አለ አንድነት አመጣኻቸው፡፡ በፊት ግን እንዲህ አልነበሩም፡፡  ፍጹም በማይለይ አንድነት ከአብራካችን እንደሚገኝ ልጅ አንድ አካል ነበሩ፡፡ ጌታ ሆይ ነገር ግን ለአንተ ይህ በአንድ አካል አንድ ሆኖ መኖር የተመረጠ አልነበረምና በአንተና በቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ሁለት አድርገህ ግን ደግሞ አንድ ሆነው እንዲኖረ ከአዳም ሔዋንን አስገኘሃት፡፡ እነዚህ ሁለት ሲሆኑ አንድ አንድ ሲሆኑ ሁለት ነበሩ፡፡ በአንድ ጥንድ ብዙ ጥንዶችን በመፍጠርም ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉዋት ብለህ ሥራህን ፈጸምህ፡፡ በዚህ መሐል ግን አንተን በድለን ፈቃድህን ተላለፈን ስለተገኘን ሁለት ሆኖ አንድ ሆኖ መኖር ለእኛ ፈታኝ ሆነብን፡፡ ስለዚህም  “የባልና የሚስት ሥርዐት እንዲህ ከሆነ አይጠቅምም” ላሉ ሐዋርያት ይህም ሕይወት ለተሰጣቸው ነው ብለህ መለስህላቸው፡፡ እንዲህ ማለትህ ሲሰጥ እንጂ ሳይሰጥ ይህም ጃንደረብነት ከትዳርም ይከፋል ልትለን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ሳይሰጥ ጃንደረባ መሆን አለሌ ወደ መሆን ያደርሳልና፡፡ ጌታ ሆይ እለምንሃለሁ እባክህ የሰጠኸንን ሕይወት አጣፍጥልን ትርጉሙም ገብቶኝ የምኖርበት እንዲሆን ፈቃድህ ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡ 

No comments:

Post a Comment