ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
16/05/2009
ኦ የዘለዓለም አምላክ ጌታችን ሆይ!! የሰንበት ጌታዋ የሆንኽ፣ ሰንበታችንም የሆንኽ እባክህ እኛም የሚቀዋወመንን የሥጋ ፈቃድ ጸጥ አድርገን ልባችንን የቃልህ ጽላት፣ ሰውነታችንን ማደሪያ ቤተ መቅደስህ አድርገን፤ አንተ ግዛታችን ሆነህ እኛም በእውነት ርስትህ ሆነን እኛም ሰንበት እንባል፤ አንተም በሚታይና በተገለጠ ጌታችን ሁነን ያኔ እናርፋለን እረፍታችንም የማይወሰድ ይሆንልናል፡፡ እኛ ፈቃድህን ፈጻሚዎች አንተም በእኛ የምትገለጥ ሁንልን፡፡ ስለምን እሾህና አሜካላ ታብቅልብህ ተብላ በተረገመች ምድራዊ ሥርዓት ውስጥ ወላጅ እንደሌለው ሰው ሆነን ተጥለን እንቅበዘበዛለን፡፡ ጌታ ሆይ እኛን የአንተ ከማድረግህ በፊት በአንተ ከእናታችን መኅፀን ፈጠርኸን፤ ቅዱስ ጳውሎስ እኔ እተክላለሁ አጵሎስ ያጠጣል እግዚአብሔር ግን ያሳድጋል እንዲል ሁሌም ቢሆን አንተ ከሕዋሳታችን ጋር ነበርህ በአንተ ፈቃድ አደገን እንጂ ራሳችንን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣን አይደለንም፡፡ ምርጫ ሰጠኸን ምርጫችን በወላጆቻችን እጅ በነበረበት ጊዜ እነርሱ ለአንተ ቀደሱን ልጆችህም አደረጉን፡፡ በራሳችን በቆምን ጊዜ የወላጆቻችን ምርጫ ትክክል እንደሆነ ገብቶን የወላጆቻችንን ምርጫ በምርጫችን አጸደቅነው፤ ለአንተም ሆንን፡፡ ምክንያቱም አንተ በእውነት ሰላማችን፣ እረፍታችን ሕይወታችን ነህና፡፡ ስለዚህ ጌታ ሆይ ከዚህ ዘለዓለማዊ ከሆነ ሰላም፣ እርጋታ፣ ፍቅር፣ ሕይወትና እውነት እባክህ አታውጣን በእርሱ ያመነ ወደ እረፍቱ ገብቶአል ይላልና በተግባር አንተን በመምሰል በአንተ ጥላ ሥር እንመላለሰ ዘንድ እባክህ ፍቀድ፤ ጤናችንን መልስ ልጆቻችንን ባርክ እኛንም በዓለም ከመባከን ታደገን፣ ሥራችንን ባርክ፣ ጌታ ሆይ በሁሉ የሆነብንን ታውቃለህና እርዳን ለዘለዓለም አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment