Monday, March 26, 2018

ቅዱሳን ሆይ ለምኑልን



  በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
መጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ.ም
ሰውነታችሁን በእውነት በጽድቅ ሕይወት ቤተ መቅደስ አድርጋችሁ እርሱ የሁሉ ጌታ የሆነ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስተ ቅዱሳን በሆነች ነፍሳችሁ መንገሡ የሚታወቃችሁና እርሱን አውቃችሁ እጅግ ትሑታን ሆናችሁ የምትመላለሱ ቅዱሳን ሆይ እናንተ ንዑዳን ክቡራን ናችሁ፡፡ የእናንተ ጭንቀት በሰውነታችሁ መቅደስ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ነግሦ ያለውን ጌታ አለማሳዘን የሆነ በሕሊናችሁ ውስጥ ስለምታሰላስሉት ሓሳብ እንኳ የምትጠነቀቁ ቅዱሳን ሆይ እናንተ ንዑዳን ክቡራን ናችሁ፡፡ እናንተ በሦስት አጥሮች ራሳችሁን አጥራችሁ ግርማውን እያያችሁ እንደ ቅዱሳን መላእክት በፍርሃትና በርዓድ ሆናችሁ በእርሱ ፊት ዘወትር የምትቆሙ ቅዱሳን ሆይ በእውነት እናንተ ንዑዳን ክቡራን ናችሁ፡፡ 


ሦስቱም አጥሮች እነዚህ ናችሁ፡- አንደኛው አጥር ሰይጣን መግቢያ በር እንዳያገኝ በዓለማዊው ነገር ራስ እንጂ ጅራት ያልሆናችሁበት ነው፡፡ ይህ አጥር ሰፊ በመሆኑ ዓለማዊ ፈቃድ ወደ ውስጥ እንዳይገባ የሚከላከል ነው፡፡ ሁለተኛው አጥር ልባችሁን የቃሉ ጽላት በማድረግ ልቡናችሁ በቃሉ ሙሉ የሆናችሁበትና ራሳችሁን በቅድስና ያስጌጣችሁበት አጥር ነው፡፡ ይህ አጥር ቅዱሳን መስለው የቅድስና አጥራችሁን ለማፍረስ የመጀመሪያውን አጥር አልፈው የሚመጡ ወገኖችን የምትከላከሉበት ነው፡፡ ሦስተኛው አጥር ግን ራሱ እግዚአብሔር ሰውነታችሁን ማደሪያ ቤተ መቅደስ አድርጎ በመለኮታዊው እሳት ያጠራችሁ አጥር ነው፡፡ እርሱን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሰይጣን ከማይደርስበት ሰማያዊ ስፍራ አኑሯችኋል ያለበት ሰማያዊ ሥፍራ ነው፡፡ በምድር ሆናችሁ በሰማያዊ ሥርዓት ሕያዋን ከሆኑ ቅዱሳን ጋር የምትኖሩ የዚህን ዓለም አኗኗር በዚህ ምክንያት የዘነጋችሁ ቅዱሳን ሆይ ከጠባቂ መላእክቶቻችን ይልቅ ዘመዶቻችሁ ነንና በጸሎታችሁ ወደ ቅድስና ማማ እንወጣጣ ዘንድ በጸሎትና በጦም በንባብ እንዲሁም በቅድስና ምልልስ ጽሙድ በመሆን ጌታችንን ደስ እናሰኘው ዘንድ ስለ እኛ ለምኑልን፡፡

No comments:

Post a Comment