Wednesday, January 23, 2019

በዓመፃ ገንዘባችሁ እወቁበት


በመ/ ሽመልስ መርጊያ
 14/05/2011
ልቡናችሁን መቅደሱ አድርጋችሁ በእርሱ ፍቅር ከብራችሁ የምትኖሩ በክርስቶስ ወንድሞቼና እኅቶቼ የሆናችሁ ወዳጆቼ ሆይ እንደው አንድ ሐሳብ ወደ ሕሊናዬ መጣና ሳወጣው ሳወርደው ለምን ከእነርሱ ጋር አብሬ አልጋራውም አልኩና እነሆ አልኳችሁ፡፡
ተወዳጆች ሆይ በእውን እንደ ሰው ምስኪንና የራሱ ያልሆነውን የእኔ ብሎ ዕውር ድንብሩን የሚጓዝ አለን ? የሚደንቀው ግን እርሱ በራሱ አርአያና አምሳል የፈጠረን አምላክ ባልፈጠርነውና የእኛ ባልሆነው ላይ አድራጊና ፈጣሪ አድርጎ ሾመን፡፡ ይህም ባሕርይው በእኛ እንዲከብር ገዢነቱ በእኛ እንዲገለጥ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ፍጥረቱ ላይ እንዲህ እንድንሰለጥን ማድረጉ ለሰው ልጆች የሰጠው የመጨረሻው ስጦታው አይደለም፡፡ ይህ ዓለም ለሰው ልጆች እንደ ድርጎ የተሰጠ እንጂ መሠረታዊም አልነበረም፡፡ በአባታችን በአዳም በእናታችን በሔዋን ውስጥም እንዲህ ዓይነት ሐሳብ አልነበረም፡፡ ያኔ በገነት ለማየትና ለመብላት መልካም ሆነው የተሰጡ አትክልትና አዝዕርት እንዲሁም እንስሳት ሁሉ ለመኖር አስፈላጊዎች አልነበሩም፡፡ ስለዚህ ዲያብሎስ በእነርሱ ላይ ይሰለጠኑ ዘንድ በተሰጣቸው ላይ የተንኮል ድሩን ማድራት አልፈቀደም፡፡ ነገር ግን እርሱ አፍቃሪያችን በጊዜ ሂደት እርሱ በፈቀደው ጊዜና ሰዓት እርሱን ወደ መመሰል አምጥቶ አማልክት እንደሚያደርገን በዲያብሎስ ዘንድ የታወቀ ነበር፡፡ ስለዚህ ዲያብሎስ ያለ ጊዜው አምላክ የመሆን ምኞትን አስቀድሞ በሔዋን ሲቀጥል በአዳም ልቡና ውስጥ አሳድሮ ከአምላክ ለያቸው፡፡ እኛም በእነርሱ ምክንያት ወደዚህች ድርጎው መሠረታዊ ነገር ወደ ሆነባትየእለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬብለን እንድንጸልይ ወደ ተገደድንባት ምድር ተጣልን፡፡

 ወዳጆቼ እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም የዚህ ዓለም ሀብትና ክብር እንዲሁም ስልጣን እንደ ጥላ ኀላፊ እንደሆነ ጌታችን አስተምሮናል፡፡ ለዚህች ዓለም ፍጻሜ አላት፡፡ አንድ ቀን ባልጠበቅናት ቀንና ሰዓት አንቀላፍተን ሳለን ድንገት እንደ ሰም ቀልጣ እንደ ክርስታስ ተጠቅልላ ሥራችንና እኛ ብቻ ቀርተን በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ እንቆማለን፡፡ ስለዚህ ጌታችን ዓለምንና በዓለም ያሉትን አትውደዱ አለን፡፡ ዓለምን የሚወድድ የእግዚአብሔር ጠላት ነው አለን፡፡ በዚህ ምድር ባፈራችሁት የአመፃ ገንዘባችሁ ወዳጆችን ለራሳችሁ አፍሩ ብሎ አስተማረን፡፡ እንዴት ሲባል ሰማያዊ መዝገብ ላደረጋቸው ለድሆች፣ ለችግረኞች እንዲሁም ለአቅመ ደካሞች፣ ወላጅ ላጡ ልጆች፣ ጧሪ ቀባሪ ለሌላቸው አረጋውያን በመስጠት ወዳጆችን አፍሩ አለን፡፡ ድሆችና ችግረኞችም በፈንታቸው ከእነርሱ ዘንድ የተረፈውን ይሰጡአችኋል፡፡ በእነርሱ እጅ የሚቀበላችሁ ደግሞ ስራብ አብልታችሁኛል፣ ስታመም ጎብኝታችሁኛል፣ ስታረዝ አልብሳችሁኛል፣ ስታሠር ጎብኝታችሁኛል ብሎ የሚያመሰግናችሁ ጌታችሁ መድኀናችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው እንጂ እሊህ ድሆች አይደሉም፡፡ እነዚህ ድሆች ስለሰው ልጆች ሲል ራሱን ባዶ አድርጎ ደሃ የሆነውን ጌታችንን መስለውታል፡፡ እንዲህም ስለሆነ ቅዱስ ጳውሎስ - “የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ፤ በትክክል እንዲሆን፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም።”(2ቆሮ.814-15) ስለ ቃሉ ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡
ተመልከቱ ወዳጆቼየእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላሲል ምን ማለቱ ነው? የድሆች ትርፋቸው ምንድን ነው ማን ነው? ክርስቶስ አይደለምን? ሥላሴ አይደለምን? በትንሣኤ እናንተ የአባቴ ብሩካን የሚባሉትና የተዋረደው ሥጋቸውን ለውጦ የራሱን እንዲመስል የሚያደርገው እርሱ አይደለምን? ይህ ለድሆች ለችግረኞች ለታመሙት፣ ለታሠሩት እንደ ጸጋ ነው፡፡ ራሱን ዘለዓለማዊ ስጦታ ያደረገውን ክርስቶስን እና ቅዱስ ጳውሎስበአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍያለውን እስቲ አነጻጽሩት ወዳጆቼ? በእውን የሚነጻጸሩ ወይም ለንጽጽር የሚቀርቡ ናቸውን? እናም ወገኖቼ በዚህ ምድር ከናቅናቸው ከገፋናቸው ካላሰብናቸው በሰቆቃ ከሚኖሩት ዘንድ ያለውን ሀብት እርሱም ከርስቶስን አስቡት፡፡ ነገር ግን ድሆች ብቻ አይደሉም ክርስቶስን የለበሱት እኛም በመስጠት ክርስቶስን ስንለብሰው ያኔ እርሱን እንመስለዋለን፡፡ እርሱ ጌታችን ስለ ድሆች ተበዳሪ ሆኖ ዋጋችንን በሞት ወደ እርሱ በሄድንና በትንሣኤ ይከፍለናል፡፡ ዋጋችንና መንግሥታችን እርሱ ክርስቶስ ነው፡፡ እናም ወገኖቼ ብልሆች እንሁን በዓመፃ ገንዘባችን እንወቅበት፡፡ ነገ የእኛ አይደለችም የእኛም የሆነ ጊዜ የለንምና እንፍራ እንቀጥቀጥ በመንግሥቱም እጁን ዘርግቶ አንገታችንን አቅፎ እየሳመን ለእኛ ባዘጋጀው ድግስ እንድንገኝ መልካሙን ሁሉ በማድረግ እንድከም፡፡ ለእኔ ለኃጥኡ ጸልዩልኝ፡፡

No comments:

Post a Comment