Thursday, January 24, 2019

የመጥምቁ ዮሐንስ ቃል(ክፍል አንድ)



በመ/ር ሽመልስ  መርጊያ 

ቀን 17/05/2011 ዓ.ም

ጌታዬ ሆይ በኣቴ በሆነች በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ ሥራዬ አንተንና አንተን ማሰብ ብቻ ነበርና ወደ እኔ የምትመጣበትን ቀን በጉጉት እጠባበቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም ገና ስጸነስ ጀምሮ የአንተ ባሪያና መንገድ ጠራጊ እንድሆን አድርገህ ስለፈጠርኸኝ አንድ ቀን ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዳለህ አውቅ ነበርና፡፡ እናም ገና የስድስት ወር ጽንስ ሳለሁ አንተ የእለት ጽንስ ሆነህ በእንግድነት ከእናትህ ጋር ወደ እኔ ስትመጣ ስጠብቀው የነበረ ተፈጽሞአልና ሊነገር በማይችል ደስታ ውስጥ ሆኜ ተቀበልኩህ፡፡ ጌታ ሆይ በቅድስት እናትህ የሰላምታ ድምጽ እንዳንተ በማሕፀን ላለሁት ለእኔ ሰላምህን ሰጥተኸኛልና አንተን በማወቄ ዕውቀቴ ገና ከማሕፀን ሳልወጣ ፍጹም ሆነ፡፡ ምክንያቱም አንተ የዕውቀት ፍጻሜ ነህና፡፡ ስለዚህ ከአንተ ከአባትህ ከእግዚአብሔር አብ ከባሕርይ ሕይወትህ ከመንፈስ ቅዱስ ሌላ ሌላ መምህር አላስፈለገኝም፡፡
ዮሴፍ ግን አንተን አላወቀህምና እንደ እኔም በነፍስ ዓይኑ አንተን አልተመለከተህምና ድንግል እናትህን ተጠራጠራት፤ በስውር ሊተዋትም አሰበ፡፡ ያኔ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሕልም ተገልጾ የአንተን በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከእናትህ መጸነስን አበሰረው፡፡ ቢሆንም እምነቱ ሙሉ አልነበረም ምክንያቱም የነፍስ ዓይኖቹ እንደ እኔ ተከፍተው አንተን ለማየት አልበቁምና፡፡ ከአይሁድ ወገን ግን ያንተን መጸነስ ያወቀ አልነበረም፡፡ እነርሱ መጽሐፉ የሚለውን ያውቃሉ እንጂ የመጽሐፉን ቃል በእምነት አልተቀበሉትም ነበርና በእነርሱ ዘንድ መታሰብህ ፈጽሞ የለም፡፡ እኔ ባሪያ ግን የባሕርይ ሕይወትህ የሆነው መንፈስ ቅዱስ አድሮብኛልና ፈጽሜ አወቅሁ፡፡ መልአኩ ለአባቴ ጸሎቱ እንደተሰማለት መክና የነበረች የእናቴ የአልሳቤጥ ማሕፀን እንደ ተፈታች ልጅንም እንደምትወልድ በነገረው ጊዜ በመጠራጠሩ አንደበቱ ቃልን ከማውጣት መክና ነበር፡፡ ነገር ግን የአንተ ሰላም ከእኔ ጋር ነበረችና በእኔ መወለድ የአባቴ አንደበት በምስጋና ተከፈተች፡፡ እናቴንም ከአይሁድ ነቀፋ ታደግኻት፡፡ ስለዚህ ይህ ተአምር በዙሪያው ባሉ ወረዳዎችና አውራጃዎች ሁሉ ተሰማ፡፡ ነገር ግን እኔ ለአንተ የተሰጠሁ ነኝና ጊዜው እስኪደርስ ድረስ አንድም ሄሮድስን ፍራቻ አንድም እኔ አንተን በአካል ለማየት መናፈቄን ታውቃለህና ከአንተ ብቻ ጋራ እንጂ ከሌላው ጋር መዋል ማደር ዋዛ ፈዛዛ ነገር መነጋገር አልፈቀድኩምና ሰው ከማይኖርበት ከምድር አራዊትና አእዋፋት ጋር በምድረ በዳ እስከ ሠላሳ ዓመት ከስድስት ወር ድረስ ኖርኩኝ፡፡  አንተ የቀጠረክባት የመገናኛችን ቀን በቀረበች ጊዜ ከአንተ ቀድሜ በመውጣት የሰውን ልቡና በንስሐ አዘጋጅ ዘንድ በአንተ ምክንያት ለሸሸኋቸው ሰዎች ተገለጥሁ፡፡ አንተ ግርማዬ ነህና ቃሌን ሰሙኝ እኔም ኃጢአታቸውን እንዲናዘዙና ስለ ኃጢአታቸው እንዲጸጸቱ በማድረግ የኃጢአትን ሥርየት የምትሰጠውን አንተን በናፍቆት እንዲጠብቁ አደረግሁ፡፡ ያኔ በማኅፀን ያልተለየኝ የባሕርይ ሕይወትህ መንፈስ ቅዱስ ስለ አንተ፡- "እኔ በርግብ አምሳል የማርፍበት እርሱ ክርስቶስ ነው" አለኝ፡፡ ነገር ግን ገና ወደ እኔ ስትመጣ ማን እንደሆንክ አወቅኹ ስለዚህ እንዴት ፍጡር ፈጣሪን ሊያጠምቅ ይችላል ብዬ አንተን ላለማጥመቅ እንቢ አልሁ፡፡ ነገር ግን ጽድቅን ሁሉ እንፈጽም ዘንድ ግድ ነው በማለት አጠምቅህ ዘንድ አዘዘኸኝ እኔም ለአንተ ታዘዝሁ፡፡ ስትጠመቅም የባሕርይ ሕይወትህ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በራስህ ላይ አረፈ አብም በደመና ሆኖ ይህ የምወልደው የምወደው ልጄ ነው አለ፡፡ ስለዚህ ያንተ አምላክነት የእኔ ደቀ መዛሙርት በሆኑትና ሊጠመቁ በመጡት ሁሉ ዘንድ ተገለጠ፡፡

No comments:

Post a Comment