Wednesday, February 15, 2012

“እኔ በእርሱ እኔነት ውስጥ”



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
08/06/2004
ይገርማል!! እኔ እምላትን አካል የሥጋዬን ታኽል እንኳ ባለማወቄ ይደንቀኛል፡፡ እኛ  ቅዱስ ጳውሎስ “ዛሬስ በመስታወት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን” (1ቆሮ.13፡12) እንዳለው ያህል እንኳ ያላየናት እኔ የምንላት መንፈሳዊት ረቂቅ አካል  አለችን ፡፡ ነፍሴ ምን እንደምትመስል እንደማላቃት እንዲሁ እኔ የምላት አካሌን አለማወቄ እንዴት የሚያሳፍር ነገር ነው ጃል!! ነገር ግን እኔ ያመጣሁት ሳይሆን እግዚአብሔር አምላክ በድንቅ ቸርነቱ ከእኔ የሰወራት ናት፡፡ በዚህ ምድር በቅድስና ለመኖር ከተጋሁ በመንፈስ ቅዱስ መነጽርነት ልክ መላእክትን እንደማየት ላያትና ቅዱስ ጳውሎስ “በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን ዛሬ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደታወቅሁ አውቃለሁ”(1ቆሮ.13፡12) እንዳለው አያታለሁ!!
እኛ በቅድስና የተጋን እንደሆነ በዚህ ምድር ሳለን እንደ ቅዱስ ጳውሎስ እኔነታችንን በድንግዝግዝታ ልንመለከታት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ካልተጋን ልክ እንደባለ ጠጋው ነዌ በሲኦል ሳለን ማየታችን አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ እውቀቶች የተለያዩ እውቀቶች ናቸው፡፡ በቅድስና ተግተን በመኖራችን እኔነታችንን ማወቃችን ለእኛ ለክብር ሲሆን ላልተጉቱ ግን ለኩነኔ ነው፡፡ እነርሱ በዚያን ጊዜ የሚመለከቱት እኔ የሚሉዋት ረቅቅ አካላቸው ሰይጣንን መስላ ነው፡፡ እኛ ግን እኔነታችንን የምናገኛት ክብር ይግባውና ክርስቶስን መስላ ነው፡፡

ጸሎትና ጽሙና(ከሶርያ ቅዱሳን አንዱ)


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
07/06/2004   
ወንድሜ ሆይ ጸሎት ሲባል የጸሎት ቃላትን ብቻ መድገም አድርገህ አንዳታስበው ፤ ወይም የጸሎት ቃላትን በማጥናት የሚማሩት አድርገህ እንዳትቆጥረው ፡፡ እውነታው ይህ አይደለም ፤ ተገቢ የሆነ ጸሎት በመማር ወይም የጸሎት ቃላትን በመድገም የምታገኘው እንዳልሆነ እንድትረዳ እፈልጋለሁ ፡፡ እርሱ ቃሎችን አሳክተህና አሳምረህ ልመና የምታቀርብለት ሹም አይደለምና ፡፡ ጸሎት የሚቀርብለት እርሱ መንፈስ ነው ፡፡ ስለዚህም እርሱ መንፈስ ነውና ጸሎትህ መቅረብ ያለበት በመንፈስ ነው ፡፡
እግዚአብሔር የሚፈቅደውን ጸሎት ለመፈጸም ድምፅ ማውጣት የሚጠበቅበት የተለየ ቦታ የለም ፡፡ ጌታችንም ስለዚህ ሲያስተምር “በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል ፡፡” ሲል እንዲሁም  ወደ እርሱ ለመጸለይ የተለየ ስፍራ እንደማያስፈልግ ሲያረጋግጥ “በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል ፡፡” ብሎአል(ዮሐ.፬፥፳፩) ስለምን እኛ በመንፈስ መጸለይ እንደሚገባንም ሲያስረዳ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ብሎ ገልጾልናል ፡፡ (ዮሐ. ፬፥፳፬)ለእርሱ የሚቀርብለት ምስጋና በመንፈስ የሚቀርብ መንፈሳዊ መሆን አለበት ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም መንፈሳዊ ጸሎትንና መዝሙራትን በተመለከት እንዴት መፈጸም እንዳለባቸው ሲያስተምር “እንግዲህ ምንድን ነው? በመንፈስ እጸልያለሁ በአእምሮም እጸልያለሁ ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ በአእምሮም እዘምራለሁ ፡፡”(፩ቆሮ.፲፬፥፲፭)ብሎናል ፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር ጸሎትና ልመናን በሚያቀርብበት ጊዜ በመንፈስና በአእምሮ መሆን እንዳለበት አስገንዝቦ ጽፎልናል፡፡