ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
07/06/2004
“ወንድሜ ሆይ ጸሎት ሲባል የጸሎት ቃላትን ብቻ መድገም አድርገህ አንዳታስበው ፤ ወይም የጸሎት ቃላትን በማጥናት
የሚማሩት አድርገህ እንዳትቆጥረው ፡፡ እውነታው ይህ አይደለም ፤ ተገቢ የሆነ ጸሎት በመማር ወይም የጸሎት ቃላትን በመድገም
የምታገኘው እንዳልሆነ እንድትረዳ እፈልጋለሁ ፡፡ እርሱ ቃሎችን አሳክተህና አሳምረህ ልመና የምታቀርብለት ሹም አይደለምና ፡፡
ጸሎት የሚቀርብለት እርሱ መንፈስ ነው ፡፡ ስለዚህም እርሱ መንፈስ ነውና ጸሎትህ መቅረብ ያለበት በመንፈስ ነው ፡፡
እግዚአብሔር የሚፈቅደውን ጸሎት ለመፈጸም ድምፅ ማውጣት የሚጠበቅበት የተለየ ቦታ የለም ፡፡ ጌታችንም ስለዚህ
ሲያስተምር “በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል ፡፡” ሲል እንዲሁም ወደ እርሱ ለመጸለይ የተለየ ስፍራ እንደማያስፈልግ ሲያረጋግጥ “በእውነት
የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል ፡፡” ብሎአል(ዮሐ.፬፥፳፩) ስለምን እኛ
በመንፈስ መጸለይ እንደሚገባንም ሲያስረዳ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ብሎ ገልጾልናል ፡፡ (ዮሐ. ፬፥፳፬)ለእርሱ የሚቀርብለት
ምስጋና በመንፈስ የሚቀርብ መንፈሳዊ መሆን አለበት ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም መንፈሳዊ ጸሎትንና መዝሙራትን በተመለከት እንዴት መፈጸም
እንዳለባቸው ሲያስተምር “እንግዲህ ምንድን ነው? በመንፈስ እጸልያለሁ በአእምሮም እጸልያለሁ ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ በአእምሮም
እዘምራለሁ ፡፡”(፩ቆሮ.፲፬፥፲፭)ብሎናል ፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር ጸሎትና ልመናን በሚያቀርብበት ጊዜ
በመንፈስና በአእምሮ መሆን እንዳለበት አስገንዝቦ ጽፎልናል፡፡
ቃል አውጥቶ ስለመጸለይ ግን
አላወሳም ፡፡ ምክንያቱም መንፈሳዊ ጸሎት ከአንደበት ይልቅ ከልብ የሚቀርብ
ነውና ፡፡ መንፈሳዊ ጸሎት በከንፈር ከሚቀርቡ ጸሎታትና በድምፅ ከሚሰሙ መዝሙራት ይልቅ እጅግ ጥልቅ ነው ፡፡
አንድ ሰው በዚህ መልክ በሚጸልይበት ወቅት ጸሎት በአንደበት ከሚያቀርበው ሰው ይልቅ በተመስጦ ይነጠቃል ፡፡
መንፈሳውያንና ቅዱሳን መላእክት ከሚገኙበት በመገኘት ልክ እንደ እነርሱ “ቅዱስ” “ቅዱስ” “ቅዱስ” እያለ ያመሰግናል ፡፡
ነገር ግን ይህ ሰው ከእንዲህ ዐይነት ጸሎት ወጥቶ ድምፅ አውጥቶ ወደ መጸለይ ከተመለሰ ከመላእክት ግዛት በመውጣት እንደተራ
ሰው ይሆናል ማለት ነው ፡፡
ድምፅ በማውጣትና በአካል እንቅስቃሴ የሚዘምር በቀንም በሌሊትም
እንዲህ በማድረግ ይጽና ፡፡ ከዚህ ይልቅ በፍጹም ተመስጦ ሆኖ በመንፈስና በአእምሮ የሚዘምር ሰው ግን መንፈሳዊ
መላእክትን ይመስላቸዋል ፡፡ መንፈሳዊያን መላእክት በክብር ከቅዱሳን ይልቃሉ ፡፡
አንድ ሰው እንደ ችሎታው መጠን በውጭ በሚገለጥ እንቅስቃሴ አምልኮቱን የሚፈጽም ከሆነ ማለትም የሚጾም ፣ ድምፅን
አውጥቶ የሚዘምር፣ተንበርክኮም ለረጅም ጊዜ የሚጸልይ፣ በትግኀ ሌሊት የጸና፣መዝሙረ ዳዊትን ደጋግሞ የሚጸልይ ከሆነ ፣ በድካም
አብዝቶ ልመናውን የሚያቀርብ ፣ በተአቅቦ የጸና ፣ የረባ ምግብን የማይመገብ ከሆነና እንዲህ ዓይነቶችን ተግባራት የሚፈጽም ከሆነ ልቡናው እግዚአብሔር ወደ ማሰብ ያመራል ፡፡
ይህ ሰው እሳትን የተላበሰ ፣
ለስሙ የሚንቀጠቀጥ ፣ በሁሉ ሰው ፊት ትሑት ፣ የሰውን ድክመትና የእርሱን ጥንካሬ እያስተዋለ እንኳ ሰው ሁሉ ከእርሱ የተሻለ
እንደሆነ የሚያስብ ፣ እርሱ የተናቀና አመንዝራ ሰው እንደሆነ ፣ እንደ ሆዳም፣ ወይም እንደ ሰካር ራሱን የሚቆጥር ሰው ይሆናል
፡፡ እንዲህም ሆኖ በትሕትና ሆኖ ሥራውን ይፈጽማል ፡፡በውስጣዊ ማንነቱ ሰው ሁሉ ከእርሱ እንደሚሻል ይቆጥራል ፤ አንድ
ኃጢአተኛን ሰው ቢመለከት እንደ ግብዝ ሰው ሳይሆን ከልቡ ወደ እርሱ በመቅረብ “እባክህ ስለእኔ ጸልይልኝ ፤ በእግዚአብሔር ፊት እንደ እኔ ኃጢአተኛ
ሰው በምድር ላይ የለም ፤ እኔ ብዙ በደልን ፈጽሜአለሁ ፣ ከእነዚህ ኃጢአቶቼ መካከል የአንዱንም እዳ እንኳ መክፈል ተስኖኛል”
ይለዋል ፡፡ እነዚህንና እኔ ከጠቀስኩአቸው የሚልቁትን የፈጸመ ሰው ቅዱሳን መላእክት ለእግዚአብሔር የሚዘምሩትን ዝማሬ ለመዘመር
የበቃ ይሆናል፡፡
እግዚአብሔር ዝምታን ይወዳል ፤ እርሱ በዝምታ ውስጥ ሆኖ ለራሱ የሆነውን መዝሙር ለራሱ ያቀርባል ፡፡ በዚህ ቦታ
የአንደበትን ዝምታን እየተናገርኩ አይደለሁም ፡፡ አንድ ሰው በመንፈስና በአእምሮ እንዴት መጸለይ እንደሚችል ሳይረዳ እንዲሁ
ዝም የሚል ከሆነ የዚህ ሰው አእምሮ ያለፍሬ ይሆናል ፡፡
አእምሮውም በክፉ ሰይጣናዊ አሳቦች ይሞላል ፡፡ እንዲህ ዐይነት ሰው በውጭ የሚታየውን ጥሞናን እየተገበረ ያለ ሰው እንጂ
በመንፈስና በአእምሮ እንዴት መዘመር እንደሚችል የማያውቅ ሰነፍ ሰው ነው ፡፡
እንዲህ ዐይነት ሰው በውስጣዊ
አንደበቱ የሚነገረውን ክፉ ሰይጣናዊ አሳብ እንዴት ማስቆም እንደሚችልም የማይረዳ ሰው ነው ፡፡ ውስጣዊ ማንነትህን ልክ ክፉና
ደጉን እንዳለየ መንፈሳዊ ሕፃን ልትመለከተው ይገባሃል ፡፡ ሕፃን መናገር የማይችልና እንዴት መናገር እንዳለበት የማያውቅ
እንደሆነ ሁሉ እንዲሁ በአእምሮው ሕፃን የሆነም ሰው እንዲሁ ምን መናገርና
ምን ማሰብ እንዳለበት የማያውቅ ሕፃን ነው ፡፡ …ስለዚህ የአንደበት ብቻ ዝምታ አለ ፤ እንዲሁ መላው አካልን ዝም ማሰኘት አለ ፡፡ የነፍስ ገንዘብ የሆነ ዝምታ አለ ፤
የአእምሮ ገንዘብ የሆነ ዝምታ አለ ፤ እንዲሁ የመንፈስ ዝምታ አለ ፡፡ የአንደበት ዝምታ ክፉን ከመናገር መከልከል ብቻ ሊሆን
ይችላል ፡፡ አካልን ሁሉ ዝም ማሰኘት መቻል ግን የስሜት ሕዋሳቶች ሁሉ በማንኛውም ስሜት ያልተያዙ እንደሆነ ያሳያል ፡፡
የነፍስ ዝምታ ክፉ የሆኑ አሳቦችን ካለማመንጨት የተነሣ ገንዘብ የምናደርገው ዝምታ ነው ፡፡ የአእምሮ ዝምታ ደግሞ
አእምሮ አጥፊ የሆነ አሳብን ወይም ተንኮልን ያላመነጨ አንደሆነ ነው ፡፡ የመንፈስ ዝምታ ማዕረግ ላይ የደረሰ ሰው ፍጡራን
በሆኑ መንፈሳዊ አካላት የተነሣ የሚከሰተውን ስሜታዊነት የተቋረጡለት እና የእርሱ እንቅስቃሴ ብቻውን በሕያው እግዚአብሔር
የሚመራ ስለሆነ ግሩም በሆነ ዝምታ የተከበበ ሰው ነው ፡፡
ከንግግር ወደ ጽሙና ለመድረስ ብዙ እርከኖችን ማለፍ ይጠበቅብሃል ፡፡ ወደ እነዚህ ማዕረጋት አንተው ራስህ ካልደረስክ
አታቃቸውም ፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ማዕረጋት ፈጽሞ የራቅህ እንደሆነ የተሰማህ ከሆነ ፣ ባለህበት በመጽናት በፍቅር ድምፅህን አውጥተህ ለእግዚአብሔር
ጸሎትህን አቅርብ ፡፡ የንስሐ መዝሙር ዘምር ፣ ከፍቅር ማዕረግ እስክትደርስ ድረስ በአገልግሎት ጽና ፡፡ ከሚያስፈራው
እግዚአብሔር ዘንድ መልካሙን በመሥራት ቁም ፡፡ እንዲህ ካደረግኽ በመንፈሳዊው ተፈጥሮህ በኩል እርሱን ወደማፍቀር ትመጣለህ ፡፡ እንዲህ እንዲሆን እርሱ በአዲስ መልክ
እንፈጠር ዘንድ ራሱን ስለእኛ አሳልፎ የሰጠው ነውና ፡፡
እናም እኔ ላንተ ትጸልየው ዘንድ የጻፍኩልህ ጽሑፍን በምትጸልየው ጊዜ እንዲሁ በአንደበትህ ብቻ ትደግማቸው ዘንድ
የሰጠሁ እንዳይመስል እወቅ ፡፡ ራስህንም ለጸሎት ታዘጋጅበትም ጭምር ነው ፡፡ እኔ ትጸልየው ዘንድ የሰጠሁህን ጽሑፍ ከሰውነትህ
ጋር አዋሕደህ ወደ ሥራ ካላመጣኻቸውና በሰው ፊት የእግዚአብሔር ሰው ሆነህ ካልታየህ በቀር እነርሱን በአንደበትህ ብቻ
በመድገምህ የምታገኝባቸው አንዳች ጥቅም የላቸውም ፡፡ ለእርሱ
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን
No comments:
Post a Comment