Wednesday, March 14, 2012

ትምህርተ ድኅነት (ክፍል ሁለት)


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
06/07/2004
እግዚአብሔር ቃል ሥጋ ማርያምን የመልበሱ ምክንያት ምንድን ነው ?
የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ ማርያምን የመልበስ ምክንያትን በተመለከት ቅዱሳን አባቶች በተለይ ቅዱስ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል ፡-
“በፍቅር እጆቹ ያበጀውን ፍጥረት በሰይጣን ተንኮል በመሰናከሉ ጠፍቶ እንዲቀር ማድረግ ርኅሩኅ የሆነው የእግዚአብሔር ባሕርይ አልፈቀደም ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እርሱ ፈታሔ በጽድቅ ኰናኔ በርትዕ ነውና እርሱ ራሱ የፈረደውን ፍርድ ማስቀረት ባሕርይው አልፈቀደም፡፡ እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ እግዚአብሔር ቅን ፈራጅ ባላስባለው ነበር፡፡ ስለዚህም በአዳምና በሰው ልጆች ላይ የተፈደውን ፍርድ ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለድና ራሱ ፍርዱን በራሱ ላይ በማድረግ በሰው ልጆች ላይ የፈረደውን ፍርድ በራሱ አስወገደው” ይለናል ፡፡በእርግጥ ይህን በተመለከተ ቅዱስ ጳውሎስ “ኀጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” ብሎ ይገልጠዋል፡፡(ዕብ.1፡3)

ትምህርተ ድኅነት(ክፍል አንድ)


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
05/07/2004
ድኅነት የሚለው ጥሬ ትርጉሙ አንድ ጤናማ ያልሆነን አካል ወደ ቀደሞው ጤንነቱ መመለስ የሚለውን ትርጉም የሚሰጠን ቃል ነው፡፡ እንደ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፅንሰ አሳብ ደግሞ ከኃጢአትና ኃጢአት ካመጣው የነፍስም የሥጋም ሕመም መፈወስ ማለት ነው፡፡ ድኅነቱም የሚፈጸመው በቤተ ክርስቲያን በሚፈጸሙ ምሥጢራት ነው፡፡ እነዚህ ምሥጢራት ከክርስቶስ ጋር ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖረን ያበቁናል፡፡ ስለዚህም ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ የተፈጸመልንን የማዳን ሥራ ለማስረዳት ስትል እንደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “እርቅ”(reconciliation) ወይም “ቤዛ” (redemption)  ወይም እንደ ፕሮቴስታንቱ “መቀደስ”(Justification) የሚሉትን ቃላት አትጠቀምም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ቃላት በክርስቶስ የተፈጸመልንን የማዳን ሥራ አሟልተው ሊያስረዱ የሚችሉ ቃላት አይደሉምና፡፡ እርቅ ስንል በሁለት ጠበኞች መካከል የተደረገን መስማማትንና ወዳጅነትን የሚያስረዳን ቃል ሲሆን ቤዛ ስንል ደግሞ አንድ እስረኛን ወይም ባለእዳን ዋጋ ከፍሎ ማስለቀቅ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ቃላት በውጭ ሊፈጸሙ የሚችሉትን ድርጊቶችን ሊያስረዱ የሚችሉ ቃላት እንጂ አንድ አካል ወደ መሆን መምጣትን የሚያስረዱ ሆነው አናገኛቸውም ወይም በድኅነት ሥራ የሁለቱን ወገን ተሳትፎ አሟልተው የሚያስረዱ ቃላት አይደሉም ፡፡


 መቀደስም ቢሆን ኃጢአትን ከመሥራት ተከልክሎ በቅድስና ሕይወት መመላለስን የሚያስረዳ ቃል ነው ፡፡ እንደውም እንደ ፕሮቴስታንቱ ዓለም አስተምህሮ አንድ ሰው ሊጸድቅ የሚችለው በእምነት እንጂ በሥራ አይደለም ፡፡ እንዲህም ስለሚሉ ክርስቶስን በተግባር ላለመምሰል ፈቃደኞች አለመሆናቸውን እንረዳለን ፡፡
እኛ ኦርቶዶክሳውያን ግን ሰው ሊድን የሚችለው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው ፤ ነገር ግን ጸጋውን ለመቀበል የግድ እምነትና ምግባር ይዘን ልንገኝ ያስፈልገናልን ብለን እናስተምራለን ፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያናችን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ጋር ያለንን የእኛን ተሳትፎ እና ከእርሱ ጋር የተፈጸመውን ፍጹም አንድነት ለማስረዳት ስትል ድኅነት(Salvation or Sotoria) የሚለውን ቃል አብዝታ ትጠቀማለች፡፡ ይህን ቃል መጽሐፍ ቅዱስ በሐዲስ ኪዳን ብቻ  የክርስቶሰን የማዳን ሥራ ለመግለጽ ሲል ከአርባ ጊዜ በላይ ተጠቅሞበታል፡፡ 
 በክርስቶስ የማዳን ሥራ ላይ የእኛ ተሳትፎ የምንለውም፡- በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር በሞቱ መተባበራችንን ፣  በትንሣኤውም ተካፋዮች መሆናችንን ፣ ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ መቀበላችንን እንዲሁም በቤተክርስቲያን ከሚፈጸሙ ሌሎችም ምሥጢራት ተካፋዮች መሆንን ፣ በተጨማሪም በተግባራዊ ምልልሳችንም እርሱን መስለን በመገኘታችንም ጭምር ነው ፡፡ ከምሥጢራት ያልተሳተፈ ወይም በተግባራዊ ምልልሱ እንደ ክርስቶስ ፈቃድ ያልኖረ ሰው ድኖአል ብላ ቤተክርስተያን አታስተምርም ፡፡ ስለዚህም  በክርስቶስ ያገኘነውንና በእርሱ የማዳን ሥራ የእኛ ሚና ምን እንደሆነ ለማስረዳት ስትል ቤተክርስቲያን ድኅነት የሚለውን ቃል ትጠቀማለች ፡፡ ይህንንም የተለመከተውንም አስተምህሮ ትምህርተ ድኅነት ብላ ሰይማዋለች ፡፡  
ቅድስት ቤተክርስቲያን ትምህርተ ድኅነት ስትሰጥ ከጥንተ ተፈጥሮአችን በመነሣት ነው ፡፡ ምክንያቱም ድኅነታችን ከአፈጣጠራችን ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ ነው ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ በራሱ መልክና ምሳሌ ፈጠረው ፡፡ ፈጥሮም ካበቃ በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ “እኛስ የክርስቶስ ልብ አለን”(ቆሮ.2፡16) እንዲል የእግዚአብሔርን አሳብንና ፈቃድ ያውቅና እንደ እርሱ ፈቃድና አሳብ ሥራውን ያከናውን ዘንድ የሕይወት እስትንፋስ የተባለውን መንፈስ ቅዱስ በንፍሃት አሳደረበት ፡፡ በንፋሃት ለአዳም የተሰጠው እስትንፋስ የተባለው መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ እንረዳም ዘንድ ወንጌላዊው ዮሐንስ ጌታችን በሐዋርያት ላይ መንፈስ ቅዱስን በንፋሃት ማሳደሩን “እፍ አለባቸው ፡- መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ” በማለት ገልጾልን እናገኛለን ፡፡ (ዮሐ.20፡22) እንዲህም ስለሆነ ሥልጣኑ የተሰጣቸው ካህናት አዲስ ተጠማቂን  ካጠመቁት በኋላ እፍ በማለት “መንፈስ ቅዱስን ተቀበል” በማለት ሰውነቱን የጌታ ቤተመቅደስ እንዲሆን ያበቁታል ፡፡  
እንዲሁ በንፍሃት በአዳም ላይ ያደረው መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ይገልጥለት ዘንድ ነው ፡፡ በዚህ ታግዞ አዳም ዓለምን መግዛት ፍጥረታትን ማስተዳደር ቻለ ፡፡ እንዲህ ቢባልም ግን መንፈስ ቅዱስ በአዳምና በሔዋን ነጻ ፈቃድ ላይ ጣልቃ ይገባል ማለት ግን አይደለም ፡፡ ይህ እውነታ መንፈስ ቅዱስ በተቀበልነው በእኛ ክርስቲያኖች ላይ የሚታይ እውነታ ነው ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ሰውነት ውስጥ ከትሞ አለ ፡፡ ነገር ግን እኛ ለነፍሳችን  እንደነፍስ ነፍስ በመሆን እንዲመራን ፈቃደኞች እስካልሆንን ድረስ በሰውነታችን ይኑር እንጂ አንዳች ሥራን ሳይሠራ በዝምታ ይቀመጣል ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ነጻ ፈቃዳችንን ያከብራል ፡፡
ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእኛ ሰውነት ውስጥ ሥራውን እንዲሠራ ከፈቀድን ለእኛ እንደ ልብ ሆኖ የእግዚአብሔርን ፈቃድና አሳብ ያለአንዳች መደነቃቀፍ እንድንፈጽም ሲረዳን እናገኘዋለን ፡፡ እውቀታችንም ቅዱስ ጳውሎስ “ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም በመንፈስ የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም”(1ቆሮ.2፡14) እንዲል  ከፍጥረታዊው ነፍስ የተለየ እጅግ የጠለቀና ቅዱስ ነው ፡፡
 እንዲሁ እግዚአብሔር አምላክ አዳምንና ሔዋንን ጥንት ሲፈጥራቸው ነጻ ፈቃድ በመስጠት አክብሮአቸው ነው ፡፡ ነጻ ፈቃዳቸውንም ይተገብሩባት ዘንድ ክፉና ደጉን የምታሳውቀውን ተክል በገነት መካከል አኖረ ፡፡ “በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ … አንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም ፡፡”(ዘፍ.3፡3)ብሎ ፈቃዱን ገለጠላቸው ፡፡ የእርሱ ፈቃድ ክፉና ደጉን ከሚያሳውቅ ተክል እንዳይበሉ እንደሆነ ነገር ግን ላለመብላት እንዳልተከለከሉ ቢበሉት ግን ሞትን እንዲሞቱና ከእርሱም እንዲለዩ አሳወቃቸው ፡፡    
ነገር ግን አዳምና ሔዋን በውስጣቸው ያደረውን የመንፈስ ቅዱስን ፈቃድ ቸል በማለት በራሳቸው ማስተዋል ተደግፈው ከእነርሱ በክብር በእጅጉ የሚያንሰውን የእባብን ምክር በማዳመጥ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ ክፉና ደጉን ከሚያሳውቀው ዕፀ በለስ በሉ ፡፡በዚህም ምክንያት መንፈስ ቅዱስ ከእነርሱ በመለየቱ ከእግዚአብሔር አምላክ ጋር የነበራቸው ኅብረት ተቋረጠ ፡፡ ስለዚህም በእነርሱ ምክንያት እግዚአብሔርን የምንመስልበት አርአያ ተጎሳቆለ ፣ ሞት በእኛ ላይ ሠለጠነብን ፣ ከሕያዋን ቦታ ከንግሥናችን ሥፍራ ከገነት ተሰደደን ወደ ተፈጠርንባትም ምድር ተመለስን ፣ ምድርም በእኛ ምክንያት ተረገመች ፣ ጽድቅንም መፈጸም ተሳነን ፣ ማስተዋላችን ተወገደ ፣ ድንቁርና ወረሰን በዚህም ምክንያት ክፉ ለሆነው ለሰይጣን ፈቃድ ተገዛን ፡፡
ቢሆንም እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ ከገነት አውጥቶ ወደዚች ምድር መስደዱ ስለጠላው አልነበረም ፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሔርን ፈቃድ መውጣት ምን ያህል ከክብር እንዳዋረደው ተረድቶ እንዲጸጸትና በንስሐ ወደ እርሱ እንዲመለስ በመፍቀዱ ነው ፡፡ እግዚአብሔርም የአዳምን ክፉ ምርጫ ስለሚያውቅና በኋላም እንዲጸጸት ስለተረዳ የሰውን ዘር ሁሉ ሊያድን ሰው እንደሚሆን እርሱን ያሰነካከለውንም ሰይጣን በሚለብሰው ሰውነት ድል እንዲነሣውና ወደ ቀደመው ክብሩ እንደሚመልሰው ጌታችን “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘሩዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ ፡፡”(ዘፍ.3፡15) ብሎ አስቀድሞ ተናገረ ፡፡ ይህንንም የእግዚአብሔርንም አሳብ አዳም ተረዳ ፡፡  
 በአንተ የተባለው ሰይጣንን ነው ፣ በሴቲቱ የተባለው በድንግል ማርያም ወይም በቤተክርስቲያን ነው ፣ በዘርህ ሲል የዲያብሎስ  የግብር ልጆችን ሲሆን ፣ በዘርዋ የተባለው ክርስቶስ  ነው ፡፡አንድም የቤተክርስቲያን ልጆችን ነው ፡፡ ይህን በራእይ.12፡17 “ዘንዶው በሴቲቱ ላይ ተቆጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የጠበቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ ፡፡” በሚለው ኃይለ ቃል ወይም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርሱዋም እናታችን ናት …እኛም ወንድሞች ሆይ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን ፡፡”(ገላ.4፡26-31)ብሎ ባስተማረው ትምህርቱ ማረጋገጥ ይቻላል ፡፡ ከዚህም በኋላ ነበር አዳም አጋሩ ትሆን ዘንድ ለተሰጠቸው ሴት “ሔዋን” ብሎ ስም ያወጣላት ትርጓሜውም የሕያውን ሁሉ እናት ማለት ነው ፡፡ ከእርሱ ወገን ከሆነችው ከቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር በሥጋ በመወለድ አዳምንና ልጆቹን ወደ ቀደመ እሪናቸው እንዲመልሳቸው በማወቁ ነበር ሔዋን ብሎ ስም የሰጣት ፡፡ የአዳምንም እምነት የተመለከተ ሥላሴ እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሰውን ከቀድሞው ክብሩ በላቀ መልኩ እጅግ እንደሚያከብረው ሊያረጋግጥለት “ እነሆ አዳም መልካሙንና ክፉውን ለማወቅ  ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ”(ዘፍ.3፡ )ማለቱ ፡፡
ይህም የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ ማርያምን በመልበስ አዳምና ልጆቹን ማዳኑ አይቀሬ መሆኑን የሚያሳይ ኃይለ ቃል ነው ፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስን ዳግማዊው አዳም ብሎ ሲጠራው አላፈረም “ፊተኛው አዳም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ ተብሎ ተጽፎአል ኋለኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ ፡፡” አለን ፡፡ (1ቆሮ.15፡45)