በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
16/05/2004
እነሆ ታላቅ የሆነ ለሰዎች ልጆች መዳን የሚጠቅመውና
ትርጉም ያለው በአምላክ የተፈጸመው ታላቁ ምልክት የታየው በምድር
ላይ እንጂ በሰማያት ከመላእክት ጉባኤ አይደለም፡፡ እርሱ ራሱ በነቢዩ “ጌታ ራሱ ምልክትን ይሰጣቸኋል እነሆ ድንግል ትፀንሳለችው
ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች”(ኢሳ.7፡14) እንዲል ታላቅ የሆነው ምልክት የታየው በምድር ነው፡፡ ሰማያውያን መላእክት ራሳቸው እንኳ ይህ ታላቅ የሆነ ምልክት ለማየት ሲሉ ጌታ ከተወለደበት ግርገግም ተገኙ፤ "ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ" እያሉ በምድር ዝማሬን አቀረቡ፡፡ ነገር ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ “ታላቅ ምልክት በሰማያት ታየ ፀሐይን ተጎናጽፋ ጨረቃን ተጫምታ በራሱዋም ላይ ዐሥራ
ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች”(ራእ.12፡1)ሲል ስለ ጌታ ልደት ብቻ መናገሩ አልነበረም፡፡ ይህ ምልክት
ከልደት እስከ ዕረገት በጌታችን ሥጋዌ የተፈጸሙትን የድኅነት ሥራዎችን ሁሉ የሚጠቀልል ነው፡፡እነዚህ የድኅነት ሥራዎች በምድር ይፈጸሙ እንጂ በሰማያዊው አምላክ የተፈጸሙ ናቸውና ፍጹም ሰማያዊያን ናቸው፡፡ ያም ማለት በቦታና በጊዜ የሚወሰኑ አይደሉም፤ ዘለዓለማውያንና ዘመን የማይቆጠርላቸው ናቸው፡፡ ምክንያቱም ዘመን በማይቆጠርለት አምላክ የተፈጸሙ ናቸውና፡፡ እነዚህን የድኅነት ሥራዎች ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሰውነት የከወናቸው ናቸው፡፡