Sunday, July 6, 2014

ቤተ ኦርቶዶክስ


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/10/2006 ዓ.ም

ኦርቶዶክስ ስንል በክርስቶስ መሠረትነት፣ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ተብላ፣ በመንፈስ ቅዱስ አስተማሪነት፣ ለሐዋርያትና ለነቢያት በተሰጠው ፍጹም በሆነው በማይናወጥና ፍጻሜ በሌለው ግን መሠረት ባለው እግዚአብሔራዊ አስተምህሮ ላይ የተመሠረተችውን፣ በሰዎች ፖለቲካዊ ጥማት ቤተ ክርስቲያን በሚባል ሽፋን ብዙ የእምነት ድርጅቶች ሳይመሠረቱ በፊት፣ ያለች በተለይ 451 በፊት ያለውን የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ይዛ የቆየች እምነት ማለታችን  ነው፡፡ በዚህ መሠረት ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን እንደመጣ መንግሥቱ የሆነች ቤተ ክርስቲያንን የሰው ሁሉ መዳን የምታገለግል አድርጎ በደሙ እንደ መሠረታት መጠን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዓለማቀፋዊት ናት፡፡ በእርሱዋ ውስጥ ግሪካዊ አይሁዳዊ የሚል የዘር ልዩነት ሴት ወንድ ብሎ የጾታ ልዩነት የሌለባት በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር በመቀበርና በአዲስ ሕይወት በመነሣት ሕያው በሆነው መንፈስ ቅዱስ  የምትመራ በልዕልና የሚኖርባት እምነት ናት፡፡
ከዚህ የተነሣ ኦርቶዶክስ ስንል መሠረቱዋ መጻሕፍትን ያጻፈው መንፈስ ቅዱስ ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተብራሩትንና የታወቁትን ግን ያልተገለጡትን እውነታዎች በሰውነታችን ባደረው ሕያው በሆነው መንፈስ ቅዱስ በሚሰጣት ማስተዋል የምትረዳና መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሁለተኛ የእውቀት ምንጭ አድርጋ የምትቀበል ናት፡፡