Sunday, July 6, 2014

ቤተ ኦርቶዶክስ


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/10/2006 ዓ.ም

ኦርቶዶክስ ስንል በክርስቶስ መሠረትነት፣ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ተብላ፣ በመንፈስ ቅዱስ አስተማሪነት፣ ለሐዋርያትና ለነቢያት በተሰጠው ፍጹም በሆነው በማይናወጥና ፍጻሜ በሌለው ግን መሠረት ባለው እግዚአብሔራዊ አስተምህሮ ላይ የተመሠረተችውን፣ በሰዎች ፖለቲካዊ ጥማት ቤተ ክርስቲያን በሚባል ሽፋን ብዙ የእምነት ድርጅቶች ሳይመሠረቱ በፊት፣ ያለች በተለይ 451 በፊት ያለውን የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ይዛ የቆየች እምነት ማለታችን  ነው፡፡ በዚህ መሠረት ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን እንደመጣ መንግሥቱ የሆነች ቤተ ክርስቲያንን የሰው ሁሉ መዳን የምታገለግል አድርጎ በደሙ እንደ መሠረታት መጠን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዓለማቀፋዊት ናት፡፡ በእርሱዋ ውስጥ ግሪካዊ አይሁዳዊ የሚል የዘር ልዩነት ሴት ወንድ ብሎ የጾታ ልዩነት የሌለባት በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር በመቀበርና በአዲስ ሕይወት በመነሣት ሕያው በሆነው መንፈስ ቅዱስ  የምትመራ በልዕልና የሚኖርባት እምነት ናት፡፡
ከዚህ የተነሣ ኦርቶዶክስ ስንል መሠረቱዋ መጻሕፍትን ያጻፈው መንፈስ ቅዱስ ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተብራሩትንና የታወቁትን ግን ያልተገለጡትን እውነታዎች በሰውነታችን ባደረው ሕያው በሆነው መንፈስ ቅዱስ በሚሰጣት ማስተዋል የምትረዳና መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሁለተኛ የእውቀት ምንጭ አድርጋ የምትቀበል ናት፡፡

ስለዚህ በቤቱዋ በአኗኗራቸው ክርስቶስን መስለው የተመላለሱ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጣቸው ማስተዋል ብዙ መጻሕፍትን የጻፉ ቅዱሳን አሉባት፡፡  ምክንያቱም የእውቀት ምንጭ ከሆነው ከመንፈስ ቅዱስ የተቀዳ ነውና፡፡ ቢሆንም ግን እንዲህ መጻሕፍትን በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የጻፉ ብዙ ቅዱሳን እንዳሉ ሁሉ ይህን የማይወድ ሰይጣን የዘራውም ከእነዚህ ጋር ተቀይጠውና ተደባልቀው እናገኛቸዋለን፡፡ እነዚህ ግን ለአንድ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ለመሰናከሉ ምክንያት አይሆኑትም፡፡  ምክንያቱም እውነትን የሚገልጥ መንፈስ ቅዱስ ለአእምሮው ማስተዋልን በመስጠት እውነተኛውን ከሐሰተኛው እንዲለይ ያግዘዋልና፡፡ ስለዚህም ነው ጌታችን “የመንግሥተ ሰማያት ደቀ መዝሙር የሆነ ጻፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል”(ማቴ.13፡52) ያለበት ምክንያት፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን  ለቁጥር የሚያታክቱ እጅግ ብዙ መጻሕፍት ከሐዋርያት ጀምሮ እስከ 451 ከዚያም በኋላ በዚህች እምነት ውስጥ ያሉ የጻፉአቸው ወይም በዚህች እምነት ውስጥ ሳይኖሩ ግን ክርስቲያን መስለው የሰይጣን ውላጅ በመሆን እንክርዳድን የዙሩ የክፉ ልጆች መጻሕፍትም አሉ፡፡
ይህ እንዲሆን ጌታም የጌታ ባሮች የሆኑት የሐዋርያት ፈቃድ ባይሆንም ሰይጣን ይህን እንደሚያደርግ የሚውቅ አምላክ እንደ ኦሪታዊያን በመጽሕፍት ብቻ ሕይወት የሚገኝ መስሎን እንዳንሰነካከል መንፈስ ቅዱስን በእኛ ላይ አሳደረ፡፡ ለአንድ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን እነዚህን መጻሕፍት የመንግሥተ ሰማያት ደቀ መዝሙር እንደሆነው ጻፊ ከመዛግብቹ አሮጌውን (የማይጠቅመውን) አዲሱን (የሚጠቅመውን) መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠው ማስተዋል አንጓሎ ይለያቸዋልና መኖራቸው ቢጎረብጠው እንጂ አያሰነካክሉትም፡፡ ምክንያቱም የሚበልጠውን ይዞአልና  መንፈስ ቅዱስ እርሱን የሚመራው ነውና እነርሱም ባይኖሩ እንኳ መንፈስ ቅዱስ በመጻሕፍት የተጻፉትን እውነታዎች በልብ ጽላት ጽፎለት ስለሚገኝ እንደ ትልቅ ጉድለት አድርጎ አይቆጥረውም፡፡ በዚህም ምክንያት ነው አይሁድ እነጴጥሮስና ዮሐንስ “በግልጥ እንደተናገሩ ባዩ ጊዜ መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ ሰዎች እንደ ሆኑ አስተውለው አደነቁ”(ሐዋ.4፡13) ተብሎ የተጻፈልን፡፡ እንዲሁም ጌታ “አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንደምትናገሩ አትጨነቁ በእናንተ የሚናገረው የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና፡፡” ብሎ አስተምሮናል(ማቴ.10፡19-20) ስለዚህ ብዙ በመንፈስ ቅዱስ የተጻፉ መጻሕፍት አሉን፡፡ እነርሱ ትክክለኛ መሆናቸውን በውስጣችን ያደረው መንፈስ ቅዱስ ይገልጥልናል፡፡ እንዲሁ ትክክለኛ ያልሆኑትን አሮጌዎችን የማይጠቅሙትንም አንጓለን እንድልንለያቸው የሰይጣን ክፉ ሥራን እንድንመለከትና እንድንጸየፈው መንፈስ ቅዱስ የሰይጣን የሆኑትን እንድንለያቸው ያደርገናል፡፡   

No comments:

Post a Comment